የም ዞን ተፈጥሯዊ መስህብ
በየም ዞን ተፈጥሯዊ፣ ታሪካዊና ባሀላዊ ተብለው የሚመደቡ በርካታ የቱሪስት መስህብ ዓይነቶች ይገኛሉ፡፡
ተፈጥሯዊ
የቦር_ተራራ

የቦር ተራራ በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል በየም ዞን የሚገኝ ሲሆን ከአዲስ አበባ 271 ኪ.ሜ ከዞኑ ዋና ከተማ ሳጃ በ32 ኪሎ ሜትር እና ከፎፋ ወረዳ በ5 ኪ.ሜ ርቀት ላይ ይገኛል።አራት ቀበሌዎችን ማለትም ሾሸርና አልማማ፣ሰሙ አዋሾ፣ላይኛው ከሸሊ እና ሸሞና መተሎን ያዋስናል፡፡ከባህር ወለል በላይ 2939 ሜትር ከፍታ ያለው ሲሆን በዞኑ ከሚገኙ ተራሮች ትልቁ ነው፡፡ የተራራው አናት በአራቱም አቅጣጫ ያሉ አጎራባች ዞኖችን ማለትም የጉራጌን፣ የሀዲያን፡ የከንባታን እንዲሁም የጂማ ዞንን በርካታ ስፍራዎች በተጨማሪም ግልገልግቤ ቁጥር 1 ሀይድሮ ኤሌክትሪክ ኃይል ማመንጫ ግድብን ወደ ቁጥር 2 የሚያስኬደውን አስገራሚ ጠመዝማዛ መንገድ መመልከት የሚቻልበት ምቹ ሁኔታ አለው፡፡ ሰንሰለታማው የቦር ተራራ በታታሪው የየም ህዝብ የአፈርና ውኃ ጥበቃ ሥራ ተሰርቶበት ሌላ ተጨማሪ ውበት ተላብሷል።የብሔረሰቡ አባላት በአንድነት በየ አመቱ ጥቅምት 17 ወጥተው ከተለያዩ እፅዋት መድኃኒት የሚለቅሙበት ዓመታዊ የመድኃኒት ለቀማ የሚከናወ ነው በዚሁ የቦር ተራራ ላይ መሆኑ ልዩያደርገዋል፡
የሰሙ_አዋሾ_ዋሻዎች

የሰሙ አዋሾ ሰው ሰራሽ ዋሻዎች በየም ዞን ከሚገኙ ሰው ሰራሽ ዋሻዎች መካከል አብዛኛዎቹ የሚገኙት በዚህ ስፍራ ሲሆን ከዞኑ ዋና ከተማ ሳጃ በ43 ኪሎ ሜትር ርቀት በፎፋ ወረዳ ሰሙ አዋሾ ቀበሌ ውስጥ ነው፡፡ዋሻዎቹን የአጎራባች ገዥዎች ግዛታቸውን ለማስፋፋት በሚያነሱት ግጭት ጠላትን ለመከላከል፣ለማጥቃትና ራሳቸውን፣ ልጆቻቸውን እንዲሁም ውድ የሆነው ንብረቶቻቸውን ለመሸሸግ ይጠቀሙበት ነበር፡፡በወቅቱ ከ150 በላይ ዋሻዎች የተቆፈሩ ቢሆንም በናዳ፣ በጎርፍ እና በተለያዩ እንቅስቃሴዎች አሁን ላይ ቁጥራቸው ከበፊቱ ቀንሷል፡፡ አንዳንዶቹ ዋሻዎች ባለ አንድ ክፍል ሌሎቹ ደግሞ ባለ ሁለት ክፍል ዋሻዎች ሲሆኑ ባለ ሁለት ክፍሎቹ አንዱ የከብቶች ማደሪያ ሌላው ደግሞ የሰውና የቁሳቁስ ማስቀመጫ በመሆን ያገለግሉ ነበር፡፡ በዋሻዎቹ ውስጥ መኝታ፣ መደብ ለመቀመጫነት እና ግርግዳው ተቦርብሮ ለዕቃ መደርደሪያነት መዘጋጀቱ እጅግ ድንቅ የሚያስብል እና ግርምትን የሚፈጥር ነው፡፡
የዞፍካር_ትክል_ድንጋይ
የዞፍካር ትክል ድንጋይ በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል በየም ዞን የሚገኝ ሲሆን ከአዲስ አበባ በ265 ኪ.ሜ ከዞኑ ዋና ከተማ ሳጃ በ 26 ኪ.ሜርቀት ላይ በፎፋ ወረዳ የሚገኝ መስህብ ነው።የትክል ድንጋዮቹ ያሉበት ቦታ መጠሪያው “ዞፍካር’’ ይባላል፡፡ ቦታው በብሄረሰቡ ዘንድ በዘመኑ ታላላቅና ታዋቂ የሚባሉት የዕምነት ተቋማት ከመፈጠራቸው በፊት ቀብር ይፈፀምበት ነበር በቦታው ላይ ቀብር መፈፀም የተጀመረበት ጊዜና ዘመን በውል ባይታወቅም በቦጊቦ ዘመነ መንግሥት(የየም የመጨረሻ ንጉስ) በዚህ ቦታ ላይ ቀብር ይፈፀም እንደ ነበር ይነገራል፡፡ በዚህም ቦታ ቀብር ይፈፀም የነበረው ከ1888 ዓ/ም በፊት ማለትም የፎፋ ደብረ መድሃኒአዓለም ቤተክርስቲያን ከመቋቋሙ በፊት ሲሆን እዚህ አካባቢ ያሉት ድንጋዮች በየቀብር ቦታው ላይ ለምልክት የቆሙ መሆናቸውን የመረጃ ምንጮች ይናገራሉ፡፡ በአጠቃላይ በስፍራው ከ211 በላይ ቁጥር ያላቸው ትክል ድንጋዮች ይገኛሉ፡፡
ወማ_ፍል_ውኃ

በርካታ አይነት የቱሪዝም ዘርፎች አሉ ከነዚህም የቱሪዝም ዘርፎች አንዱ የስፓ ቱሪዝም ነው፡፡ #ስፓ_ቱሪዝም_ማለት ምህጻረ ቃል ሲሆን #sanus_per_aqum/ #health_through_water/ ይህ የቱሪዝም አይንት በአሁኑ ወቅት በአለማችን በከፍተኛ ደረጃ እየተለመደ የመጣ ዘርፍ ነው ፡፡ በሀገራችን የሚገኙ በርካታ ሆቴሎችና ሪዞርቶች ሰው ሰራሽ ስፓ በማዘጋጀት ለተጠቃሚዎቻቸውበማቅረብ ላይይገኛሉ፡፡ በማዕከላዊ_ኢትዮጵያ_ክልል_በየም_ዞን ይህ አይነቱ የቱሪዝም እንቅስቃሴ እንደምካሄድ ያውቃሉ?
እንኪያስ ካላወቁ አንድ እንበሎት የፍል ውሃው ስያሜ #ወማ ይባላል ከዞኑ ዋና ከተማ ሳጃ በ75 ኪ.ሜ ርቀት ላይ በቶባ ወረዳ በሶሩና ጎን ቀበሌ ውስጥ ይገኛል፡፡ ተፈጥሮ ይህን ፍል ውኃ የለገስን በሁለት ዓይነት መልክ ነው፡፡ የመጀመሪያው ከረግረጋማ አረንጓዴ ጨፌ መሰል ሳር እና አለት ውስጥ ከተለያየ ቦታ የሚፈልቅ ፊል ውኃ ሲሆን ይህን ሳይበርዙ መጠቀም አይደለም መንካት የማይሞከር ነው፡፡ ለፈጣሪ ምስጋና ይግባውና ይህንን አይቶ ሙቅ ውሃውን እንደለገሰን ሁሉ ቀዝቃዛውንም ከፍሉ ውሃ አጠገብ እንካቹ በርዛችው ተጠቀሙት በማለት ለግሷል። እዚህ ላይ ከአንድ ቦታ እነዴት ቀዝቃዛና ፍል ውሃ ይፈልቃል ብላችሁ እንዳትጠይቁን ምክንያቱም ለፈጣሪ የሚሳነው ነገር የለምና፡፡ በመሆኑም ቀዝቃዛውንና ፍል ውሃውን በመቀላቀል #በመታጠብ የተለያዩ የቆዳ በሽታንና የመገጣጠሚያ ቁርጥማቶች ለመከላከል ሲሆን #በመጠጣት የውስጥ ደዌን እንዲሁም #በመታጠን የመተንፈሻ አካላትን ህመም ለመከላከል ይጠቀሙበታል ፡፡ ፍል ውኃው በተንጣለለው የግቤ ወንዝ አጠገብ በመሆኑ ጉማሬዎች በብዛት በመመልከት መንፈሶን ያድሳሉ፡፡ ይህን ፋል ውኃ በጳጉሜ ወር በመቶዎችና በሽዎች የሚቆጠሩ ሰዎች ከዞኑ እና ከአጎራባች ዞኖች ለቆይታቸው የሚሆነውን ስንቃቸውን አንግበው ወደዚህ ስፍራ በመጓዝ ይጠቀሙበታል፡፡
ሳሞ_ኤታ
የየም ብሔረሰብ በርካታ በሽታዎችን የሚፈውስ ባህላዊ የህክምና ዘዴ አለው፡፡ የተለያዩ መድኃኒት አዋቂዎች በብሔረሰቡ በስፋት የሚገኙ ሲሆን በአካባቢ የሚገኙ ዕፅዋትን በባህላዊ ሙያ ቀምመው በማዘጋጀት ለተለያዩ የሰውም ሆነ የእንስሳት በሸታዎች መድኃኒት ያዘጋጃሉ ፡፡ ጥቅምት 17 በርካታ የብሄረሰቡ አባላት በነቂስ ወጥተው ከቦር ተራራ ላይ ባህላዊ መድኃኒት የሚለቅሙበት ቀን ነው፡፡ይህ ተራራ የተመረጠበት ምክንያት ተደርጎ የሚቀርበውም የመጀመሪያው የማለዳ ፀሐይ የሚገኘው በዚህ ስፍራ ላይ በመሆኑ በተራራው ላይ የሚገኙት መድኃኒቶች የመፈወስ አቅማቸው ከፍተኛ ነው ተብሎ ስለሚታመንበት ነው፡፡በየዓመቱ ተለቅሞ የሚቀመመው መድኃኒት “ሳሞ ኤታ” (የከረመ መድኃኒት) በመባል ይታወቃል፡፡ የመድኃኒት አዋቂዎች ለተለያየ በሽታ ታማሚዎች ህክምና የሚሰጡት የታማሚውን ሁኔታ በቅድሚያ በመጠየቅ፣በመዳሰስና በመመልከት ካረጋገጡ በኃላ የመድኃኒቱን አጠቃቀምም ሆነ መጠን ጭምር በመግለፅ ነው፡፡ መድኃኒት ለቀማውና ባህላዊ ጤንነትን የመጠበቅ ዘዴ ከጥንት ጀምሮ ከትውልድ ትውልድ ሲተላለፍ የመጣ ሲሆን የባህላዊ መድሃኒት ለቀማው፣ ቅመማውና ህክምናው በስፋት በብሄረሰቡ ውስጥ ሰርፆ የቆየ ሀገር በቀል ዕውቀት ነው፡፡
ብርብርሳ ፏፏቴ
የብርብርሳ ፏፏቴ የሚገኘው በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል በየም ዞን ዋና ከተማ ሳጃ ሲሆን ከአዲስ አበባ 235 ኪ.ሜ ከወልቂጤ 89 ኪ.ሜ ርቀት ላይ ይገኛል።ብርብርሳ ፏፏቴ በየም ዞን ከሚገኙ ተፈጥሮአዊ መስህቦች ውስጥ አንዱ ነው። ፏፏቴ ከአዲስ አበባ ጅማ በሚወስደው ዋና የአስፓልት መንገድ 600 ሜትር ገባ ብሎ በዞኑ ዋና ከተማ ሳጃ ውስጥ የሚገኘው ፏፏቴ በመሆኑ በቀላሉ ገባ ብሎ ጉብኝቶ ለመውጣት በጣም ምቹ ነውከፏፏቴው ጅርባ በሰው እጅ የተጠረቡ እንጂ ተፈጥሮ ያበጀቻቸው የማይመስሉት ዓለቶች እንዲሁም ፏፏቴውን ያጀቡት ቋጥኞች የፏፏቴውን ውበት አጉልተውታል።