Skip to main content

ሀዲያ ዞን

የሀዲያ ዞን ታሪካዊ መስህቦች

                             መግቢያ

ቱሪዝም ማለት ጎብኚዎች/ቱሪስቶች በሚያደርጉት ጉዞ ጉብኝትና ቆይታ በሚያካሄዱት እንቅስቃሴና ግንኙነት የሚፈጠር ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ክስተት ሲሆን የቱሪዝም ኢንዱስትሪ መስህቦች፣ ትራንስፖርትና አኮሞዴሽን (ማረፊያና መመገቢያ) ተብለው በሚታወቁ መሠረታዊ ምሰሶዎች ጥምረት ላይ የተመሠረተ ነው። የቱሪስት መስህቦች የሚባሉት የጎብኚዎችን ቀልብ መማረክ የሚችሉ ማንኛውም ዓይነት ቦታ፣ ሁኔታ፣ እንቅስቃሴ፣ ቁሶች እና ሌሎችንም ሆኖ በተናጠል የሚጎበኙ የመስህብ ሀብቶች ባህላዊ፣ ታሪካዊና ተፈጥሯዊ በመባል በሦሥት ይመደባሉ። 

ሀገራችን ኢትዮጲያ የበርካታ የቱሪዝም ሀብቶች ባለቤት እንደመሆንዋ ለቱሪዝም ኢንዱስትሪ ልማት ሰፊ ዕድል አላት። የሀገሪቱ የቱሪዝም ሀብቶችም በሁሉም የሀገሪቱ ክልሎችና አካባቢዎች የተሠራጩ ናቸው። ከዚህ የተነሳ ከኢትዮጲያ ርዕሰ-ከተማ (መዲና) ከአዲስ አበባ በቅርብ ርቀት በሚገኘው የሀድያ ዞን ውስጥ ምንም እንኳን በዓለም አቀፍ ደረጃ የመመዝገብ ዕድል ባያገኙም በዓይነትም ሆነ በብዛት በርካታ የሆኑ የቱሪዝም ሀብቶች ይገኛሉ።

የሀድያ ዞን በጂኦግራፊያዊ መገኛው ከታደለው መልካም ዕድል የተነሳ ከሀገሪቱ ማዕከል ከአዲስ አበባ በስተደቡብና በስተምዕራብ አቅጣጫ ወደሚገኙ የቱሪስት መዳራሻዎች የሚጓዙ ቱሪስቶች የዞኑን ዋና ከተማ ሆሳዕናን ለጉዞ ዕረፍት እና/ወይም ለአዳር አገልግሎት ይጠቀሙታል። 

እነዚህ ቱሪስቶች በሀድያ ዞን ውስጥ ጥቂት ቆይታ አድርገው የመስህብ ሀብቶቹን የመጎብኘት ፍላጎት ቢኖራቸውም እንኳ በዞኑ ውስጥ የሚገኙ የቱሪስት መዳራሻዎች በአግባቡ ለምተው ወደቱሪዝም ገበያ ያልገቡ በመሆናቸውና የቱሪዝም ሀብቶቹ ባልለሙበት ሁኔታም ቢሆን ለቱሪስቶቹ በቂ መረጃ ስለሌላቸው በከተማዋ የጉዞ ዕረፍት እና/ የአዳር አገልግሎት ብቻ ተጠቅመው ይሄዳሉ። ይህንን ችግር ለመቅረፍና ቱሪስቶች ቀልባቸው የሚወድላቸውን የመስህብ ሀብቶች መርጠው የሚጎበኙበት ደረጃ ድረስ ለማልማት እንዲረዳ በዞኑ ከሚገኙ የቱሪስት መዳረሻዎች መሀከል የአራቱን ማለትም የኦሊደ-ኡሩልቾ ዋሻዎች፣ የሲራሮ ባዳዋቾ ሐይቆች፣ የሀብቾ ሜዳ የማህበረሰብ ፓርክ፣ እና የከላላሞ ተራራ የማህበረሰብ ፓርክ የቱሪስት መዳረሻዎችን  ናቸዉ፡፡ 

 

በሀድያ ዞን የሚገኙ የቱሪስት መዳረሻዎች 

የሀድያ ዞን በማዕከላዊ ኢትዮጲያ ክልላዊ መንግሥት ከሚገኙ ዞኖች አንዱ ሲሆን ከኢፌዴሪ ርዕሰ - ከተማ ከአዲስ አበባ በስተደቡብ ምዕራብ አቅጣጫ ይገኛል፡፡ የሀድያ ዞን በምሥራቅ ከሀላባ ዞን፣ ከስልጤ ዞንና ከኦሮሚያ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት፤ በሰሜን ከጉራጌና ከስልጤ ዞኖች፤ በምዕራብ ከየም ዞንና ከኦሮሚያ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት፤ እንዲሁም በደቡብ ከከምባታ ዞን፣ ከጠምባሮ ልዩ ወረዳና ከደቡብ ኢትዮጲያ ክልላዊ መንግሥት ጋር ይዋሰናል፡፡ ሆሳዕና ከተማ የዞኑና የማዕከላዊ ኢትዮጲያ ክልላዊ መንግሥት ዋና ከተማ ሲሆን ከኢፌዴሪ ርዕሰ - ከተማ ከአዲስ አበባ በቡታጅራ በኩል በ232 ኪ/ሜትር፣ በወልቂጤ በኩል ደግሞ በ282 ኪ/ሜትር ላይ ይገኛል፡፡

የሀድያ ዞን የቆዳ ስፋት 3652.20 ካሬ ኪሎ ሜትር ይሆናል፡፡ ዞኑ ከባህር ጠለል በላይ ከ501 ሜትር እስከ 3000 ሜትር ባለው ከፍታ ላይ የሚገኝ ሲሆን ዝቅተኛ ሥፍራው በጊቤ ወንዝ ሸለቆ፣ ከፋተኛ ሥፍራው ደግሞ በሰንጊዬ ተራራ ጫፍ ላይ ነው፡፡ የአየር ንብረቱ 19 በመቶ ደጋ፣ 68.1 በመቶ ወይናደጋ፣ እና ቀሪው 12.9 በመቶ ቆላና በረሃማ ነው፡፡ የዞኑ ዓመታዊ አማካይ የሙቀት መጠን ከፍተኛ 27.5 ዲግሪ ሴልሺየስ፣ ዝቅተኛው 12.6 ዲግሪ ሴልሺየስ ሲሆን ዞኑ በዓመት በአማካይ ከ801 ሚሊ ሜትር እስከ 1400 ሚሊ ሜትር መጠን ያለው ዝናብ ያገኛል፡፡ 

በሀድያ ዞን በ1999 ዓ.ም በተካሄደው 3ኛ ዙር የሕዝብ ሙሉ ቆጠራ ዉጤት መሠረት በ2017 ዓ.ም ወንድ 1032095፣ ሴት 1044555 በድምሩ 2076650 ሕዝብ እንደሚኖርበት ይገመታል፡፡ ከዚህ ውስጥ 317727 (15.3 በመቶ) በከተማ፣ ቀሪው 1758923 (84.7 በመቶ) ሕዝብ ደግሞ በገጠር ቀበሌያት ሰፍሮ የሚኖር ነው፡፡ በዞኑ ከሚገኘው ሕዝብ 8.5 በመቶ የኦርቶዶክስ ተዋህዶ ክርስትና፣ 75.3 በመቶ የፕሮቴስታንት ክርስትና፣ 4.3 በመቶ የካቶሊካዊ ክርስትና፣ 11.1 በመቶ የእስልምና፣ 0.2 በመቶ ባሀላዊ፣ እና 0.6 በመቶ የሌሎች እምነቶች ተከታዮች ናቸው፡፡

የሀድያ ዞን አስተዳደር በአሁኑ ጊዜ በአሥራ ሦሥት ወረዳዎችና በሰባት የከተማ አስተዳደሮች የተዋቀረ ነው፡፡ በዞኑ የሚገኙ ሁሉም ወረዳዎችና የከተማ አስተዳደሮች ኩታገጠም የተገናኙ አይደሉም፡፡ ሦሥት ወረዳዎችና የሾኔ ከተማ አስተዳደር (የባዳዋቾ አከባቢ ወረዳዎችና የከተማ አስተዳደር) ከሌሎቹ የዞኑ ወረዳዎችና የከተማ አስተዳደሮች በመሀከላቸው የከምባታ ዞን መለያ ሆኗቸው ያሉ ናቸው፡፡

በሀድያ ዞን ተፈጥሯዊ፣ ታሪካዊና ማህበራዊ ተብለው የሚመደቡ በርካታ የቱሪስት መስህብዓይነቶች ይገኛሉ፡፡ 

  1.    ፏፏቴዎች (ግሮ፣ ወምቢሌ፣ ሀብቾ፣ አገሜና ሆጄ፣ ፍንጩዋ፣ ዊሪቻሞ፣ ዓለምበቃ፣ …)፣ 

  2.    ሐይቆች (ቦዮ፣ ቡደመዳ፣ ጢሎ፣ መጨፈራ፣ ግልገል ጊቤ ቁጥር ሦሥት ግድብ)፣ 

  3.    ተራሮች (ከላላሞ፣ ሾንቆላ፣ አና፣ ቱላ፣ ሰንጊዬ፣ በርጎሳ፣ ሾኔ፣ …)፣ 

  4.    የተፈጥሮ ደኖች (ሁነሴ፣ አምበሪቾ፣ ሜጋቾ፣ ኩፈና፣ አንዲሴ፣ ጊቶሌ፣ ሀባ፣ …)፣ 

  5.    ዋሻዎች (ኦሊዳ፣ አምበሪቾ፣ ሰጠና፣ ሙሳጌሳ፣ ኡሩሊቾ፣ ሃደዬ፣ ሲቢያ፣ ቀንቅቾ፣ …)፣ 

  6.    ትክል ድንጋዮች (ኢሌ፣ ጃርሶ፣ …)፣ 

  7.    ታሪካዊ ቦታዎች (አምቼ ሾላና አካባቢው፣ ሶር አባዩው ሕድር ቤዮ (የአራቱ ወንድማማቾች ቃል ኪዳን ሥፍራ)፣ የቦዮ ረግረጋማ ሐይቅ፣))። 

  •   የአምቼ ሾላና አካባቢው በቀድሞ ዘመን በሕዝቦች እንቅስቃሴ ወቅት ከሀድያ ብሔር የሌሞ ነገድ አሁን ወደሠፈረበት አካባቢ ሲደርስ በአንድነት የሠፈረበት ቦታ ነው። አምቼ የሚል መጠሪያ የተሰጠው ሾላም በከብቶች የጋራ በረት አጠገብ የበቀለች እንደሆነ የሚነገር ሲሆን በዚህ አካባቢ ለረጅም ዘመናት የቆየ የብሐሩ የባህላዊ ግጭት አፈታትና ዳኝነት ሥርዓት ማካሄጃ የነበረና በኢትዮጲያ ዘመናዊ አስተዳደር ሥርዓት ሲመሠረትም ለአውራጃው የመጀመሪያ የአስተዳደር ማዕከል የነበረ ሥፍራ ነው፡፡ አሁንም ቢሆን የአካባቢው ነዋሪዎች ይህ የአምቼ ሾላ የሚገኝበትን ማሳ የማረስና ሰብል ሲደርስም የመሰብሰብ ሥራ ባለቤቱን በማገዝም ጭምር ከሌላው ማሳ አስቀድመው ያከናውናሉ፡፡ በማህበረሰቡ መሀከል ከአቅም በላይ የሆነ ማንኛውም ችግር ሲያጋጥም በዚህ ሾላ ሥር በመሰብሰብ አምላካቸውን ይለማመናሉ፡፡ ይህ ሥፍራ በአንሌሞ ወረዳ በምዕራብ አንሌሞ ቀበሌ የሚገኝ ሲሆን ከሆሳዕና ወደአዲስ አበባ መሥመር ከዋና መንገዱ በስተምደቡብ ምሥራቅ አቅጣጫ 23ኪ/ሜትር ያህል ይርቃል፡፡   

  •    ሶር አባዩው ሕድር ቤዮ የአራቱ ወንድማማቾች ቃል ኪዳን ሥፍራ (Soor abbayyuwi hiddi'l beyyo)፡- ይህ ሥፍራ በጊቤ ወረዳ በሆማ ከተማ አስተዳደር ክልል ውስጥ የሚገኝ ሲሆን ባዶጎ፣ ሞቾሶ፣ መስመስ እና ቦሾአና የሚባሉ የሀድያ ብሔር ተወላጅ ነገዶች አንድ ወቅት ለጋራ ሰላምና ልማት ቃል ኪዳን የፈጸሙበት ሥፍራ ነው፡፡ በዚያ ቃልኪዳን ምክንያት አራቱም ነገዶች እየተረዳዱና ለጋራ ሰላማቸው እየሰሩ ዛሬም ድረስ አብረው ይኖራሉ፡፡ በአሁን ጊዜም ቢሆን ማስረጃ ያልተገኘለት ችግር ሲከሰት እውነቱን ለማውጣጣት የተጠረጠረውን ግለሰብ በዚህ ሥፍራ የመመርመር ሥራ ይሠራል፡፡ ማንም እውነቱን ይናገራል፡፡ እውነቱን መሰወር አደጋ እንዳለው ይታመናልና፡፡ 

  •   የቦዮ ረግረጋማ ሐይቅ፡- በሐይቁ ዙሪያ ሠፍረው ባሉ የሻሾጎ ነገድ ተወላጆች አባት ቦዬ መቃብር ላይ የፈለቀ ፍል ወኃ የተፈጠረ ረግረጋማ ሐይቅ እንደሆነ ይታመናል፡፡ የሻሾጎ አካባቢ ነዋሪዎች በማህበረሰቡ ማሀከል እንደዝናብ መጥፋት፣ ወረርሽኝ መከሰት፣ የሰለም እጦትና የመሳሰሉ ችግሮች ሲከሰቱ በሐይቁ አካባቢ በመሰብሰብ አምላካቸውን ይለማመናሉ፡፡ 

አምላክ እንደሚታረቃቸውና ችግሩ እንደሚወገድላቸውም ይታመናል፡፡ በአሁን ጊዜ የሐይቁ መገኛ የሆነው ፍልወኃ ምንጭ በደለል ስለተደፈነ ሐይቁ የመጥፋት አደጋ ተጋርጦበታል፡፡ 

  1.    ዕድሜ ጠገብ የሃይማኖት ተቋማትና የሀድያ ብሔር ባህላዊ የመኖሪያ ቤቶችና ‹ነፈራ› ይገኛሉ፡፡

    ወቅት ጠብቀው ከሚከበሩ ማህበረሰባዊ ኩነቶች መሀከል፡- በሀድያ ብሔር ደረጃ በሆሳዕና ከተማ በሚገኘው ‹ሀድይ ነፈራ› የሚከበረው ‹ያሆዴ› የሀድያ ብሔር የዘመን መለወጫ በዓል፣ በየዓመቱ በጥር ወር ውስጥ የሚካሄደው በከብት እርባታ ሥራ የተሳካላቸው አርሶና አርብቶ አደሮች የከብቶቻቸው ቁጥር አንድ መቶ እና አንድ ሺህ ሲሞላ የከብቶች ማስቆጠር ሥርዓት - ‹ወገና› - ለአርቢው እውቅና መስጫ በዓል፣ እና በየዓመቱ በሆሳዕና ደብረ ገነት ቅድስት ማርያም ቤተክርስቲያን የሚከበር የ‹በዓለ-ሆሳዕና› በዓላት ይጠቀሳሉ፡፡

    ዞናችን ውብ የመሬት አቀማመጥና ማራኪ የተፈጥሮ ሀብት ያለው ፤ ዞኑ የተለያዩ የቱሪዝም ሀብቶች ማለትም ተራሮች፣ዋሻዎች ፏፏቴዎች፣ሐይቆች ደኖችና ሌሎች የቱሪስት መስህቦች የሚገኝ ዞን ነው፡፡

    ዞኑ እነዚህን ሀብቶች በማጥናት በመጠበቅና በማልማት ከትዉልድ ወደ ትዉልድ እንዲሸጋገር ለባህልና ቱሪዝም መምሪያ ተልዕኮ ተሰጥቶ እየተሰራ ይገኛል፡፡ በዚሁ መሰረት የዞኑን  ታሪክዊ፣ ታፈጥሮአዊ እና ባህላዊ መስህቦችን በማጥናት፣ በማልማትና በመጠበቅ ከትውልድ ወደ ትውልድ እንዲሸጋገር ለማድረግና እንዲሁም ለዓለም በማስተዋወቅ የዞን፣የክልሉና የአገር ገጽታ ግንባታ ላይ ተገቢውን ድርሻ እያበረከተ ከመሆኑም ባሻገር የዞኑን ገቢ በማሳደግ ከብልጽግና መሰረቶች አንዱ በመሆን  የማይናቅ ሚና በመጫወት ላይ ይገኛል፡፡ ሲለሆናም በ2017 በጀት ዓመት የኦልዳ-ዋሻ፤ በከለላሞ ተራራ የማህበራሰብ ፓርክ፤የመጨፈራ ሐይቅ፤የጢዕሎ ሐይቅ፤የቡዳመደ ሐይቅና የሀብቾ ሜደ የማህበረሰብ ፓርክ እንድቋቋም ይሄንን ረቂቅ ሠነድ በመዘገጀት ላይ ዘርፉ ይገኛል፡፡ 

        2.የኦልዳ- ኡሩልቾ ዋሻዎች መገኛና ይዘት

ልዳ ዋሻ በፎንቆ ከተማ አስተዳደርየሚገኝ ታሪካዊ ዋሻ ሲሀን ከሆሳዕና በስተሰሜን ምሥራቅ አቅጠጫ 23 ኪሎ ሜትር ይርቃል፡፡

ኦልዳ ዋሻ በጭንጎ ሰንሰለታማ ተራራ ላይ የተቆፈራ ሰው ሰረሽ ዋሻ ሲሆን ሶስት ደርቦች አሉት፡፡ የታችኛው ለእንሰሳት ማደሪያና ለምግብ ማብሰያነት እንዳገለገለ የሚጠቁሙ ምልክቶች የሉባት ሲሆን ሙከለኛው ደግሞ ለሰዎች ማደሪያነት እንዲሁም ሶስተኛው ደግሞ ርቀት አካባቢዎችን ለመቃኛት እንዳገለገለ ጠቋሚ ምልክቶች አሉት ዋሻው በውስጡ ግድግዳው የሀድያ ብሔር የቤት ውስጥ አጋጌጥኛ አያያዝ እሴቶች (ኮዶዶ፤ሎካ-----ወዘተ) አሉበት፡፡ ዋሻው ወዳ 56.2ሄ/ሬጅ የተሸፈና መሆኑንንም በከለላ ወቅት ተውቆዋል፡፡ ዋሻው ከኡሩልቾ እና ከቀርጌቾ ዋሻዎች የተሰሳራ መሆኑን አንድአንድ ጥናቶች ይጦቅመሉ

 

 

               ኡሩልቾ ዋሻ

ኡሩልቾ ዋሻ በፎንቆ ከተማ አስተዳደር የሚገኝ ታሪካዊ ዋሻ ሲሀን ከሆሳዕና በስተሰሜን ምሥራቅ አቅጠጫ 19 ኪሎ ሜትር ይርቃል፡፡

ዋሻው በኡሩልቾ ሰንሰለታማ ተራራ የተሰሰራ መሆኑን የሚየሰዩ ብዙ ጉዳዮች ይጠቅመሉ፡፡ዋሻው ታሪካዊ ዳራ ከመኖሩ የተነሰ ብከለል፤ብጠበቅና ብለመ ለቱሪዝሙ ልማት ከፈተኛ አስተዋጾኦ ይኖረል ተብሎ ይገመተል፡፡ ዋሻውም ከኦልዳ ዋሻው ጋር የተሰሰራ መሆኑንም አንድ አንድ ጥነታዊ ጽሁፎች ይጦቅመሉ፡፡

 

 

 

 

 

 

 

              

 

 

 

 

 

   የከላላሞ ተራራ ማህበረሰብ ፓርክ ልማት ሠነድ

መነሻ

የከላላሞ ተራራ ማህበረሰብ ፓርክ በቁጥር አምስት የሚሆኑ ታሪካዊና ተፈጥሯዊ የቱሪስት መስህቦችን የያዘ ነው፡፡ እነዚህም ታካዊዎቹን የአወሳ ሜዳ፣ የከላላሞ ተራራ፣ እና የቡደመዳ ሰው ሠራሽ ዋሻዎችን እና ተፈጥሯዊዎቹን የወማጌ ፏፏቴ፣ እና የጊቤ ወንዝ ሸለቆ ተፈጥሯዊ ደን ናቸው፡፡ የቱሪስት መስህቦቹ በጊቤ ወረዳ በአወሳ፣ በሙማ፣ በሜጋቾ፣ በወርቾ ዶይሰባ፣ በሀሌልቾ ቤሮ፣እና በገሰዳ ኮዳዳ ኩታገጠም ቀበሌያት ይገኛሉ፡፡

የአወሳ ሜዳ ታሪካዊ መሠረቱ በሜዳው ዙሪያ ሠፍሮ የሚኖረው የሀድያ ብሔር አካል የሆነው የባዶጎ ነገድ አባቶች በቀድሞ ዘመን የአወሳ ሜዳን ለጋራ መውጫነትና ለከብቶች ማሰማሪያነት የወል ይዞታ ሆኖ እንዲቆይ ወስነው ማቆየታቸው ነው፡፡ ሜዳውን እስከዛሬ ድረስ ሰውም ሆነ የዱር አውሬ አልቆፈረውም፡፡ ሜዳው ላይ ሳር ብቻ በቀር ዛፎችና ቁጥቋጦዎችም አልበቀሉበትም፡፡ ትውልድ ሁሉ የአባቶችን ዉሳኔ አክብሮ ያቆየውና ስፋቱ ከ200 ሄክታር የሚልቅ ታሪካዊ ቅርስ ነው፡፡ 

የከላላሞ ተራራተ ታሪካዊ መሠረቱ እንደ አወሳ ሜዳ ሁሉ በዙሪያ ሠፍሮ የሚኖረው የሀድያ ብሔር አካል የሆነው የባዶጎ ነገድ አባቶች የተራራውን ዙሪያ ገባ ለመቃኘት የሚያገለግላቸው ከፍታ ቦታ በመሆኑ ክብር በመስጠት አምላካቸውንም ለመለማመን ጭምር የቀደሱት ተራራ ነው፡፡ ተራራው በአወሳ ቀበሌ የሚገኝ የሀድያ ብሔር ባህላዊ የሳር ጎጆ ቤት የሚመስል ቅርጽ ለው ተራራ ነው፡፡ የከላላሞ ተራራ ከፍታ ከባሕር ጠለል በላይ 1880 ሜትር እንደሆነ ይገመታል፡፡

የቡደመዳ ሰው ሠራሽ ዋሻዎች በቀድሞ ዘመን በከላላሞ ተራራ ላይ በተለያዩ አቅጣጫዎች የተቆፈሩ በቁጥር ሁለት ዋሻዎች ናቸው፡፡

የወማጌ ፏፏቴ በከላላሞ ተራራ አቅራቢያ ባለው ወንዝ የሚገኝ ፏፏቴ ሲሆን በዝናብ ወራት ድምቀቱ እጅግ የሚጎላ ፏፏቴ ነው፡፡

የጊቤ ወንዝ ሸለቆ ተፈጥሯዊ ደን በአወሳ፣ በሙማ፣ በሜጋቾ፣ በወርቾ ዶይሰባ፣ በሀሌልቾ ቤሮ፣ እና በገሰዳ ኮዳዳ ኩታገጠም ቀበሌያት ምዕራባዊ ዳርቻ በጊቤ ወንዝ ሸለቆ ውስጥ የሚገኝ ሲሆን በተፈጥሮ ደኑ ክልል ወስጥ የከላላሞ ተራራ፣ የቡደመዳ ዋሻዎች፣ የወማጌ ፏፏቴ ይገኛሉ፡፡ በጊቤ ወንዝ ሸለቆ ተፈጥሯዊ ደን ውስጥ የተለያዩ ሀገር በቀል ዛፎችና ቁጥቋጦዎች፣ የተለያዩ ዝርያ አዕዋፍት፣ በርከታ ዓይነት የዱር እንስሳት፣ ዓዞና ዘንዶ ጨምሮ በርካታ የሚሳቡ ፍጥረታት በጊቤ ወንዝ ውስጥ ደግሞ ጉማሬ እንዲሁም ወደጊቤ ወንዝ መዳረሻ አካባቢ በኤሬራሞ ወንዝ ዓሳ ይገኝበታል፡፡         

የከላላሞ ተራራ ማህበረሰብ ፓርክ መገኛና ይዘት

የከላላሞ ተራራ ማህበረሰብ ፓርክ በጊቤ ወረዳ ከሚገኙት የቱሪስት መስህቦች አንዱ ነው፡፡ የጊቤ ወረዳ በሀድያ ዞን ካሉት 13 (አሥራ ሦሥት) ወረዳዎች አንዱ ሲሆን ከዞኑ ዋና ከተማ ከሆሳዕና በስተምዕራብ አቅጣጫ ይገኛል፡፡ የወረዳው አስተዳደር በ21 የገጠርና 4 የከተማ በድምሩ በ25 ቀበሌያት የተዋቀረ ነው፡፡ ዋና ከተማው ሆመቾ ሲሆን ከሀድያ ዞን ዋና ከተማ ከሆሳዕና በሞርሲጦ ከተማ በኩል በ30 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ ይገኛል፡፡ የከላላሞ ተራራ የማህበረሰብ ፓርክ በጊቤ ወረዳ ከሚገኙ ተፈጥሯዊና ታሪካዊ የቱሪስት መስህቦች አንዱ ሲሆን የከላላሞ ተራራ በአፈጣጠሩ የሀድያ ብሔር ባህላዊ የሳር ጎጆ ቤት የሚመስል ሆኖ የተራራው አናት ለጥ ያለ ሜዳ (ፕላቱ) አለው፡፡ የተራራው ከፍታ ከባህር ጠለል በላይ 1880 ሜትር እንደሆነ ይገመታል፡፡ ተራራው ዙሪያ ገባውን በቆላማና በረሃ አካባቢ የሚገኝ እንደመሆኑ የተጠቀሰው ያህል ከፍታውም ታዋቂ አድርጎታል፡፡ ተራራው ከወረዳው ማዕከል ከሆመቾ ከተማ አስተዳደር በስተምዕራብ አቅጣጫ በ15 ኪሎ ሜትር፣ ከዞኑ ማዕከል ከሆሳዕና ከተማ ደግሞ በ45 ኪሎ ሜትር ርቀት በአወሳ የገጠር ቀበሌ ምዕራባዊ ይዞታ በጊቤ ወንዝ ሸለቆ ውስጥ ይገኛል፡፡ የጊቤ ወንዝ ሸለቆ ይዞታ 200 ጋሻ(8000 ሄክታር) የሚገመት ስፋት አለው፡፡ ከዚህ ውስጥ 612 ሄክታር በኢት/ኤሌከትሪክ ባለሥልጣን ተከልሎ የዱር እንስሳት ጥበቃ ይደረግላቸዋል፡፡ በከላላሞ ተራራ የማህበረሰብ ፓርክ ይዞታ ውስጥ የወማጌ ፏፏቴ፣ የቡደመዳ ሰወ ሠራሽ ዋሻዎች፣ እና የጊቤ ወንዝ ሸለቆ ተፈጥሯዊ ደን፤ እንዲሁም በቅርብ ርቀት የአወሳ ሜዳ ታሪካዊ ቅርስ ይገኛሉ፡፡ 

 

                          የሀብቾ ሜዳ የማህበረሰብ ፓርክ 

                    መነሻ

የሀብቾ ሜዳ የማህበራሰብ ፓርክ ታሪካዊና ተፈጥሯዊ የቱሪስት መስህቦችን ያካተተ ነው፡፡ እነዚህም ታሪካዊውን የሀብቾ ሜዳ፣ የባለብዙ ከብቶች እርበታ ባለታክ የካያንቾ ልጅ የዶጆ የከብቶች ርቢ መታሰቢያ ሐውልት፣ የሀብቾ፣ የአገሜና ሆጄ ፏፏቴዎች ናቸው፡፡ እነዚሁ የቱሪስት መስህቦች በጎምቦራ ወረዳ በሀብቾ ከተማ፣ በአዴአና እና በኦርዴ ቦብቾ በሦሥቱ ኩታገጠም ቀበሌያት ይገኛሉ፡፡ 

የሀብቾ ሜዳ የማህበረሰብ ፓርክ ታሪካዊ መሠረቱ ከዛሬ አራትና አምስት ትውልድ (በገምት በ19ኛው ምዕተ ዓመት አጋማሽ) አካባቢ ተከስቶ በነበረው ድርቅና የከብቶች በሽታ ወረርሽኝ በሀገሩ አጠቃላይ የቤት እንስሳት ስላለቀ ሰዎች የወተት ተዋጽኦ በማጣት እየተጎዱ ስለነበረ በብዙ ሺህ የሚቆጠሩ ከብቶች ያሉትና ለብቻው ከብቶቹን እያሰማራ በመኖሩ ከብቶቹ ከድርቁና ከበሽታው ወረርሽኝ የተረፉለት የካያንቾ ልጅ ዶጆ  ወተትና የወተት ተዋጽኦ በማጣት ለተቸገሩት ወገኖቹ ለሆኑት ለአራት ወንደማማች ጎሳዎች ማለትም ለሸኮ፣ ለቦሻ፣ ለአባሮ፣ እና ለሀዴ ጎሳዎች ተወላጆች ወተትና የወተት ተዋጽኦ እንዲያገኙና በጋራ የከብት ርቢ ዘር እንዲሆናቸውም ጭምር ለእያንዳንዱ ጎሳ በቁጥር አንድ መቶ ጥገት ላሞችን ከነጥጆቻቸው ቆጥረው በመለየት በሥጦታ ያደሉበት ሜዳ ነው፡፡ ይህም በሀገራችን ከተለመደው በርካታ ሰዎች ለአንድ ወይም ለጥቂት ሰዎች መቋቋሚያ እርዳታ ከመስጠት በላቀ ሁኔታ አንድ ግለሰብ ለአራት ጎሳዎች (ማህበረሰቦች) መቋቋሚያ እርዳታ መስጠት የተፈጸመበት ሜዳ በመሆኑ ታሪካዊ ሥፍራ አድርጎታል፡፡ ለዚህም በሕብረተሰቡ ሜዳውን በክብር ቅርስነት ጠብቆት የቆየው ከመሆኑም በላይ በሜዳው ሰሜናዊ ዳርቻ የዶጆ የከብቶች ርቢ መታሰቢያ ሀውልት ቆሞበት ይገኛል፡፡ የሀብቾ ፏፏቴ በሀብቾ ከተማ ሰሜን ምዕራባዊ ዳርቻ በሀብቾ ወንዝ ላይ የሚገኝ ሲሆን ገምት ከ40 ሜትር የሚወርድ ፏፏቴ ነው፡፡ በፏፏቴው ዙሪያ ባለው ደን ወፎች ይገኛሉ፡፡ መልክዓ ምድሩም የተለየ ዉበት አለው፡፡

የአገሜና ሆጄ ፏፏቴዎች ከሀብቾ ከተማ በሰሜን ምዕራብ አቅጣጫ በግምት 14 ኪሎ ሜትር በኦርዴ ቦብቾ ቀበሌ በአገሜና ሆጄ ወንዞች የተፈጠሩ ፏፏቴዎች ናቸው፡፡ በፏፏቴዎቹ ዙሪያ ባለው ጥቅጥቅ ደን ውስጥ የተለያዩ የዱር እንስሳትና አዕዋፍት ይገኛሉ፡፡