በቀቤና ልዩወረዳ ተፈጥሯዊ መስህብ
በቀቤና ልዩወረዳ ተፈጥሯዊ፣ ታሪካዊና ባሀላዊ ተብለው የሚመደቡ በርካታ የቱሪስት መስህብ ዓይነቶች ይገኛሉ፡፡
ተፈጥሮዋዊ
ደቀንሺ ሞላ ፏፏቴ
ደቀንሺ ሞላ ፏፏቴ የሚገኘው በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል በቀቤና ልዩ ወረዳ ከወሸርቤ ከተማ አጎራባች ከሆነው ደቀንሺ ሞላ ቀበሌ ሰዴ በሚባል ጎጥ ውስጥ ነው።ደቀንሺ ሞላ የሚለው ቃል ትርጉሙ በቀቤንኛ ቋንቋ መገናኛ ማለት ሲሆን መጠሪያውን የሰጡት የአከባቢው ታዋቂ ሽማግሌ ሀጅ ሳኒ ሰይድ በመባል ይታወቃሉ።የፏፏቴው ርዝመት በግምት ወደ 25 ሜትር አካባቢ ይሆናል።ፏፏቴው ጎንና ጎኑ በሲሚንቶ የተገነባ በሚመስል ትልልቅ አለቶች ዙሪያውን የተከበበ ሲሆን በአከባቢው ባሉ አለቶች ላይ ዛፎች በቅለው በአየር ላይ እና በድንጋይ ላይ ተንጠልጥለው ይገኛሉ። በፏፏቴው ዙሪያ ባሉ አለቶች ላይ የተለያዩ ትላልቅ እና ትናንሽ በጣም ማራኪ የሆኑ አዕዋፋት እና የተለያዩ እንስሳቶች ድንጋዩን ፈልፍለው ይኖራሉ።ደቀንሺ ሞላ ፏፏቴ የተሸፈነው በተፈጥሮ እና ሰው ሰራሽ ደን ነው ። ይህ ደን በቀቤና ልዩ ወረዳ ውስጥ ካሉ ደኖች ውሰጥ አንዱ እና የተለያዩ የዱር አራዊቶች መኖሪያቸው ያደረጉበት ድንቅ እና ማራኪ ተፈጥሮአዊ የቱሪዝም መዳረሻ ስፍራ ነው።
የዉጥኝ ተራራ

የውጥኝ ተራራ የሚገኘው በማእከላዊ ኢትዬጵያ ክልል በቀቤና ልዩ ወረዳ ከአዲስአበባ 150 ኪሜ ከወልቂጤ ከተማ በ34 ኪሜ በርቀት ላይ ይገኛል።ይህተራራዉበቱ እጅግ ማራኪ የሆነ የተፈጥሮ አቀማመጥ ያለዉ ተፈጥሮአዊ የመስህብ ስፍራ ነዉ ፡፡በተራራዉ አናት ላይ እድሜ ጠገብ ዛፎች ፣ሜዳማ ስፍራ እድሜ አጠገብ ታሪካዊ መካነ መቃብር ፣ ልዩ ልዩ አእዋፋት እና የዱር እንስሳት ይገኛሉ ፡፡በዚህ ተራራ ላይ ሰኢድ ኑር ሁሴን በቅፅል ስማቸዉ (አባዬ) መካነ መቃብር በቆርቆሮ ታጥሮ ይገኛል ፡፡ እኚህ ሰዉ በዚያን ዘመን ታዋቂ የአከባቢ ሽማግሌ እና ከአርሲ ክፍለ ሀገር ሀይማኖታዊ ት/ምት የመጡ እንደነበር የታሪክ መዛግብት ይጠቁማሉ ፡፡ የዉጥኝ ተራራ ከጎኑ በኩል ዋሻ እነዳለዉ እና በዋሻዉ ዉስጥም ማዕድናት እንደሚገኙበት በአፈ ታረክ ይነገራል ፡፡ ከዚህ ጋር ተያይዞም በጣሊያን ወረራ ወቅት ጣሊያኖች ዋሻዉን በትላልቅ ቋጥኝ ድንጋይ እንደሸፈኑት የአከባቢዉ ነዋሪዎች ይናገራሉ ፡፡ በዉጥኝ ተራራ ላይ ዱዓ ማድረግ በፈጣሪ ተቀባይነት አለዉ ብለዉ የሚያምኑ የተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች በአሁኑ ዘመንም ወደ አካባቢዉ መጥተዉ ተራራዉን ይጎበኙታል ፡፡ በዉጥኝ ተራራ ላይ ትላልቅ እና የተለያዩ ቅርጻ ቅርጽ ያላቸዉ ድንጋዮች ይገኛሉ፡፡ በድንጋዮች ላይ ያሉ ምስሎች በድሮ ጊዜ ጣሊያን ኢትዮጵያን በወረረበት ጊዜ የጣሊያን ወታደሮች የተለያዩ የሀገራቸዉን ነገስታት ምስሎች በድንጋዮቹ ላይ ትቀርፆ ይገኛል ፡፡ ይህ የድንጋይ ቅርጻ ቅርጽ ለተራራዉ ለየት ያለ ዉበት አጎናፅፎቶታል።የሆንን የተፈጥሮ መስህብ መጎብኘት ውስጥን በሀሴት ይሞላል።
መአድነል አስራር ፏፏቴ

መአድነል አስራር ፏፏቴ የሚገኘዉ በማእከላዊ ኢትዮጵያ ክልል በቀቤና ልዩ ወረዳ በቃጥባሬ ቀበሌ ዉስጥ ነዉ ፡፡ፏፏቴው ከ አ.አ 150 ኪሎ ሜትር ከልዩ ወረዳዉ ዋና ከተማ ከወልቂጤ 15 ኪ.ሜ ርቀት ላይ ይገኛል፡፡ፏፏቴዉ መጠሪያ ስሙን ያገኘዉ ከአረበኛ እና የአማርኛ ቃላት ሲሆን ስያሜዉንም የሰጡት የቃጥባሬ ሼህ የነበሩት ሼህ ሱልጣን ኢሳ እንደሆኑ አንዳንድ ቀደምት አባቶች ይናገራሉ ፡፡ትርጉሙም መአድን ያለበት ሚስጥራዊ ቦታ ለማለት ነዉ ፡፡ፏፏቴዋ በሲሚንቶ የተገነባ በሚመስል ትላልቅ ድንጋዮች የተከበበች ናት ፡፡በፏፏቴዉ ድንጋያማ ግድግዳ ላይ አንዳንድ ዛፎች በቅለዉ ስራቸዉን በአየር ላይና በድንጋይ ላይ ተንጠልጥለዉ ይገኛሉ ፡፡ የፏፏቴዉ ዉሃ ወርዶ የሚሰበስብበት ቦታ ለተለያዩ መድሃኒት የሚዉል የምንጭ ዉሃ ይገኛል ፡፡በፏፏቴዉ ግድግዳ ላይ የተለያዩ ትላልቅና ትናንሽ ማራኪ የሆኑ አእዋፋት እና ትንናሽ እንስሳቶች ድንጋዩን ፈልፍለዉ እና በቡድን ይኖራሉ ፡፡ መአድነል አስራር ፏፏቴ የተሸፈነዉ በተፈጥሮ እና በሰዉ ሰራሽ ደኖች ነዉ ፡፡ይህ ደን በቀቤና ልዩ ወረዳ ዉስጥ ከሚገኙ አእምሮን ከሚያድሱ የተፈጥሮ መስህቦች ዉስጥ አንዱ ነዉ ፡፡
ዋቤ የተፈጥሮ ደን
ሀገራችን እንደሚታወቀው በርካታ የተፈጥሮ እና ሰው ሰራሽ ደኖች ባለቤት መሆኗ ግልፅ ነው። ከእነዚህ በርካታ እና ማራኪ ደኖች የውስጥ አንዱ የዋቤ ደን ነው።ይህ ደን በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል በቀቤና ልዩ ወረዳ ከአአ በ 150 ኪሜ ከወልቂጤ ከተማ 7 ኪሜ ርቀት ላይ የሚገኝ ሲሆን ደኑ የዋቤ ወንዝ ተፋሰስን ይዞ ረጅም ኪሎ ሜትሮችን ያካልላል። የዋቤ የተፈጥሮ ደን ስያሜውን ያገኘው (ዋሀቤ) ከሚለው የቀቤንኛ ቋንቋ ሲሆን ትርጉሙም (ውሃ ነው) ማለት እንደሆነ የብሔረሰቡ ታሪክ አዋቂዎች ያስረዳሉ። ይህ ደን በአካባቢው ከሚገኙ ደኖች በስፋቱ እና በተፈጥሮ አቀማመጡ እጅግ ለየት ያለ ወብ የተፈጥሮ መስህብ ነው። ይህ ደን በቀቤና ልዩ ወረዳ ከሚገኙ 23 ቀበሌዎች ውስጥ 7 ቀበሌዎችን ያህል ያዋስናል።
እነሱም (ቆላከባዳ፣ቃጥባሬ፣ገርባጃ፣ደቀንሺሞላ፣ወሸርቤጣጤሳ፣ጫንጮ፣ውጥኝ እና ጬካ ደመካሽ) የተሰኙ ቀበሌዎች ናቸው። እነዚህን ቀበሌዎች በተለያየ ስፋትና አቅጣጫ እየነካ የሚሄድ ጥቅጥቅ ያለ ማራኪ የተፈጥሮ ደን ነው። ይህ ደን የሚሸፍነው ርቀት 40.5 ኪ.ሜ እንደሚሆን ይገመታል።በደኑ ውስጥ በአይነታቸው፣በዘራቸው እና በቁጥራቸው እጅግ በጣም በርካታ የሆኑ እድሜ አጠገብ እና ሀገር በቀል ዛፎች ማለትም ዝግባ፣ዌራ፣ዶቅማ እና የተለያዩ የእፅዋት ዝርያዎች ይገኙበታል።እንዲሁም በርካታ ብርቅዬ የአእዋፋት ዝርያዎች መገኛ እና ለተለያዩ የዱር አራዊቶች መጠለያ ሆኖ እያገለገለ ይገኛል።ለአብነትም ያህል ጅብ፣ቀበሮ፣ከርከሮ፣ተኩላ እና የተለያዩ እንስሳቶች የመኖሪያ ስፍራ ነው።ዋቤ የተፈጥሮ ደን የአካባቢውን የአየር ሚዛን (ኢኮሎጂ) ተጠብቆ እንዲቆይ በማድረግ የልዩ ወረዳውን ብሎም የከተማውን የአየር ሁኔታ ወደ ከፍተኛ ሙቀት እንዳይቀየር የራሱ የሆነ አስተዋጽኦ እያደረገ ይገኛል።ይህንን ሰፍራ መጎብኘት ልብን በሀሴት ይሞላል።