የም ዞን ባህላዊ መስህብ
የም ዞን ባህላዊ መስህብ
ጥቅምት 17 የባህል መድሃኒት ለቀማ ስርዓት(ሳሞ-ኤታ)
መግቢያ

የሰው ልጆች ከስነ-ምሕዳር ጋር ባላቸው ቀጥታና ቀጥታ ባልሆነ ቁርኝት እና መስተጋብር ምክንያት የፈጠሩት ባህላዊ የህክምና እውቀት ወይም ሀገር በቀል እውቀት የሰውንና የቤት እንስሳትን ጤና አስጠብቆ እንዳቆዩ የሚታመን ነው፡፡ ባህላዊ መድሃኒት ምንድነው? የአንድ ማህበረሰብ በውስጡ ለሚያገጥሙት የተለያዩ ህመሞች በባህላዊ መልኩ በማዘጋጀት በፈውስነት ሊጠቀምበት የሚቻልበት መድሃኒት ማለት ነው፡፡ ስለሆነም የየም ማህበረሰብ ባህላዊ ህክምና እውቀትና ጥበብ ለሰውም ሆነ ለእንስሳት ጤና ያበረከተው ወይም እያበረከተ ያለው አስተዋጽኦ እጅግ ከፍተኛ ነው፡፡
ጥቅምት 17 በየም ማህበረሰብ ዘንድ ልዩ ትኩረት የሚሰጥበት ቀን ነው፡፡ ይህ ዕለት በህብረተሰቡ ዘንድ ልዩ ግምት የሚሰጥበት ምክንያት ለጤና ጠንቅ የሆነውን በሽታ ለመከላከልና ለማስወገድ ሲባል በባህላዊ መንገድ ጤንነትን የመጠበቅ ዘዴ ከጥንት ጀምሮ ከትውልድ ትውልድ ሲተላለፍ የመጣ በመሆኑ የባህላዊ መድሃኒት ለቀማው፣ቅመማውና ህክምናው በስፋት በብሄረሰቡ ውስጥ ሰርፆ የቆየ ሀገር በቀል ዕውቀት በመሆኑ በየዓመቱ ጥቅምት 17 የባህል መድሃኒት ከዕፅዋት (ቅጠላ ቅጠሎች፣ ስራስሮች፣ ቅርፍቶችና ከመሳሰሉት) ለቀማ የሚደረግበትና የተለቀመው ወደ መኖሪያ ሰፈር(ቤት) ተወስዶ ለሰው እና ለቤት እንስሳት የሚሆን መድሃኒት ተለይቶ ይቀመማል፡፡ የተቀመመው መድሃኒት በንፁህ ዕቃ ተቀምጦ እስከ መጪው አመት ድረስ አገልግሎት ይሰጣል፡፡ ይህ ሂደት በብሄረሰቡ ቋንቋ አጠራር "ሳሞ ኤታ" ተብሎ ይጠራል፡፡
ይህ ሳሞ-ኤታ በመባል የሚታወቀው የባህል መድሃኒት በየዓመቱ ጥቅምት-17 ቀን ማህበረሰቡ በመላው ተሳትፎ በቦር ተራራ በመውጣት እና በሌሎች በዞኑ ውስጥ በተመረጡ አካባቢዎች በአዋቂዎች ዘንድ የባህል መድሃኒት ለቀማ ስነ ስርዓት ይካሄዳል፡፡በዕለቱ የመድሃኒት ለቀማው ስርዓት በተለያዩ አከባቢዎች የሚካሔድ ቢሆንም በዋናነት በየዓመቱ የሚለቀምበት ቦታ በቦር ተራራ ነው፡፡ ይህ የተመረጠበት ምክንያት ተራራው ከፍታ ያለው በመሆኑ የመጀመሪያውን የማለዳ የፀሀይ ብርሃን ቀድሞ የሚያገኝ ሲሆን በዚሁ አካባቢ የሚፀድቁ እፅዋቶት ለበሽታ የመከላከልና ፈዋሽነት አቅም ከፍተኛ ነው ተብሎ ስለሚታመን ነው፡፡ በተጨማሪም ሎሎች አካቢዎች የማይገኙ እፅዋቶት አይነት ስለሚገኙ፡፡ ሌላው ዕለቱ የተመረጠበት ምክንያት የጥቅምት ወር ለመድሃኒት ምቹ እና ከረምት አልፎ ሁሉም እፅዋቶት ከስራስር አስከ አበባ ድረስ የእሸትነት ደረጃ ላይ የደረሰ በመሆኑ በዚህ ዕለት ሁሉም በህብረት ወጥቶ ይለቅማል፡፡
በዚህ ስፍራ የፆታ፤ የሃይማኖት፤ የዕድሜ ወዘተ…ልዩነት ሳይኖር ሰዎች ከተለያዩ አካባቢዎች ወደ ቦር ተራራ በመውጣት ይለቅማሉ፡፡ በቦታው ያሉ እንደ ‹‹ሱሉቶ››እና ‹‹ቶቱ›› ከሚባሉት የእዕፅዋት አይነቶች በስተቀር ሁሉም ይለቀማል፡፡እነዚህ የማይለቀሙትም ቢሆኑ ለጊዜው ጥናት ስላልተደረጉ እንጂ ለመድሃኒትነት አገልግሎት ባይውሉም መርዛማነት ያላቸው በመሆኑ ለሌሎች ለፀረ-ተባይ ማጥፊያና ለሌሎች አገልግሎቶች መዋል የሚችሉ ናቸው ተብሎ ይገመታል፡፡የየም ብሔረሰብ የባህል መድሃኒት አጠቃቀም አገር በቀል እሴት ከሌሎች የኢትዮጵያ ክፍሎች ለየት ያለ ፤ በተለይ በዓመት አንድ ጊዜ ብቻ ጥቅምት 17 ህዝቡ በሙሉ ወደ ተራራው በመውጣት የባህል መድሃኒት ለቀማ የሚያካይድበት ነው፡፡ በመሆኑም ይህ ሀገር በቀል እውቀት ለሀገሪቱ ለቱሪስት መስህብነት መዋል የገቢ ምንጭ መሆን የሚችል እሴት ነው፡፡ ከ60 በላይ ለሚሆኑ ዋና ዋና በሽታዎች ፍቱን የሚሆኑ መድሃኒቶች ተለቅመውና ተቀሚሞ ለሰው እና ለእንስሳት ይሠጣል፡፡ ይህ የባህል ህክምና ቅመማ ዘዴ ሀገር በቀል እውቀቱ ከቀደምት አባቶቻችን ጀምሮ በቅብብሎሽ አሁን ላለነው ትውልድ እንዲህ ባሉት ተፈጥሮ የተሰጣቸው የጥበብና የእውቀት ባለቤት የሆኑ አባቶች ዘንድ ተጠብቆ የቆየ ሲሆን ህብረተሰቡ የተለያዩ ከበሽታዎች በመፈወስ በርካታ የብዙ ሰዎች ሆነ በርካታ የእንስሳት ሕይወትን እየታደገ ያለ ሀገር በቀል እውቀት ነው፡፡
ይህ የባህል መድሃኒት ለቀማ ስርዓትና አጠቃቀም ዘዴው ዋነኛው የብሔረሰቡ መገለጫ ነው፡፡ ይህ ሀገር በቀል እውቀት የአጠቃቀም ዘዴ እና የባህል መድሃኒት አለቃቀምና የቅመማ ስርዓት፤ በአመት አንድ ጊዜ ህብረተሰቡ በአንድነት ወጥቶ ከልዩ ልዩ እፅዋት መድሃኒት የሚለቀምምበት ልምዱንና እውቀቱን በአደባባይ ልውውጥ የሚደረግበት ልዩ ትዕይንት ያለው በመሆኑ የተለየ ያደርገዋል፡፡ይሁን እንጂ ይህ ድንቅ የባህል ትይንት፤ የባህል ህክምና ልማድ፤ እውቀትና ወግ በሌሎች አካባቢዎች የሌለ እና ብቸኛው በየም ማህበረሰብ ዘንድ የሚካሄድ ሀገር በቀል እውቀት ሆኖ ሳለ በዓለም ህዝብ ዘንድ አልተዋወቀም፡፡ ስለሆነም ይህ ባህላዊ መድሃኒት ለቀማው ለቀጣዩ ትውልድ መሸጋገር ያለበት በሀገር እንዲሁም በዓለም አቀፍ ደረጃ ታውቆና ተመዝግቦ መጠበቅ ያለበት በመሆኑ በማይዳሰስ ወካይ ቅርስ ሆኖ በዩኔስኮ እንዲመዘገብ የማህበረሰቡ ጥያቄ ነው፡፡
በብሔረሰቡ በባህል መድሃኒት አወቂዎች የሚሰጡ የባህል ህክምና አገልግሎቶች ትቅቶቹ፡-
ለምሳሌ፡-
ክንታሮት ጋንግሪን
ቁርጥማት/ሳቶ/ አባላዘር በሽታ/አምሺሾ/
የአጥንት ነቀርሳ/ኬማር/ አሜባ/ባኡ/
የደም ፍላት /አርኒ ፋላ/ የደም ግፍት
የጥርስ ህመም ለተለያዩ የቆዳ በሽታዎች ወ.ዘ.ተ…
ጥቅምት 17 ባህል መድሃኒት ለቀማ ሂደት አሁናዊ ነባራዊ ሁኔታ
ዘርፉ ትኩረት ተሰጥቶ እንዲሰራ የሚያስችለውን ፍኖተ-ካርታ በማዘጋጀት የዞኑ መንገግስት በሰራው ስራ የኢፌዴሪ ጤና ጥበቃ ሚኒስቴር ሚኒስትር እና የቀድሞ ደቡብ ክልል ከፍተኛ አመራሮች በቦታው በመገኘት እንዲጎበኙ ተደርጓል፡፡ በተሰራው ሀብት ማሳባሰብ ስራ የ2 ሚሊዮን ብር ድጋፍ ተደርጎ ሳሞ-ኤታ የባህል መድሃኒት ህክምና መስጫና የጥናትና ምርምር ማዕከል መገንባት ተችሏል፡፡
በዚህ መሰረት
በማዕከሉ የተደራጁ የባህል መድሃኒት አዋቂዎችና የወገሻ ባለሙያዎች አገልግሎት እየሠጡ ይገኛሉ፡፡
በተጨማሪም በማዕከሉ ውስጥ የጥናትና ምርምር ስ ለመስራት ከዋቸሞ ዩኒቨርሲቲ እና የዞኑ መንግስት ጋር በቅንጅት በመስራት ስምምነት ላይ ተደርሷል፡፡
ስለሆነም ይህንን የማህበረሰቡን ሀገር በቀል እውቀት በጥናትና ምርምር አስደግፎ በመስራት ወደ ላቀ ደረጃ ለማድረስ እና ለቀ ትውልድ ለማስተላለፍ የሚያስችለውን ስራ ከዩኒቨርሲቲው ጋር በጋራ እየተሰራ ነው፡፡
በየዓመቱ የሚለቀምበት ቦታ ቦር ተራራ ለዚህ ተግባር ብቻ የሚውል የተከለለ እና ጥብቅ ቦታ ነው፡፡
በማህበረሰቡ ተሳትፎ በየዓመቱ ሀገር በቀል ችግኞች ተከላ ይደረጋል፡፡ እየተደረገም ይገኛል፡፡
‹‹ሳሞ-ኤታ ዘ ብሔረ የም›› በሚል ርዕስ መፅሐፍት በተስፋሁን ጥላሁን ተፅፏል፡፡ (2015 ዓ.ም)
የባሕላዊ መድሃኒት አጠቃቀም ልማድና ከዘመናዊ ህክምና ጋር የማቀናጀት አመለካከት በየም ብሔረሰብ ተተኳሪነት በሚል ርዕስ በዶ/ር ለማ ንጋቱ (ከጅማ ዩኒቨርሲቲ) የዳሰሳ ጥናት ተደርጓል፡፡(2008 ዓ.ም)
ይህ የማህበረሰቡ ሀገር በቀል እውቀት በዓለም አቀፍ የቅርስ መዝገብ በዩኔስኮ እንዲመዘገብ ለሚመለከተው አከል ጥያቄ ቀርቦ በሂደት ላይ ይገኛል፡፡