Skip to main content

የሀዲያ ባህላዊ መስህብ

                                                             የሀዲያ ባህላዊ መስህብ

የሀድያ ብሄር የዘመን መለወጫ ያሆዴ 

ያሆዴ ማለት የሀድያ ዘመን መለወጫ ክብረ በዓል ሲሆን  በወርሃ መስከረም ውስጥ የሚከበር  የሃዲያ ብሄር የማንነት መገለጫ የሆነ የአሮጌው ዓመት ማብቂያና የአዲስ ዓመት መባቻ ዘመን መለወጫ ዓውደ ዓመት  የሽግግር በዓል ነው፡፡ 

በዚህም መሰረት የባህል ሽማግሌዎች እና አባቶች በባህል አልባሳት በማጌጥ ምርቃት የሚያደርጉበት፣ ችቦ/ጦምቦራ በመያዝ ለፈጣሪ ምስጋናን የሚያቀርቡበት፣የቤታቸውንና የከብት በረታቸውን  ዙሪያ በመዞር ባለፈው ዓመት በእኛም በከብቶቻችን ላይ የነበርክ ክፉ ውጣ እያሉ ዓመቱ የሰላም የደስታ እንድሆን ጸሎት የሚያሰሙበት ነዉ፡፡ በተለይም ወጣት ወንዶችና ሴቶች ልጆችም ጭምር በአዲስ ልብስ አሸብርቀው የያሆዴን ጨዋታ በመጫወት እየበሉና እየጠጡ የሚያሰልፉበት ቀን ነው፡፡

 ዓመቱን በሙሉ በሥራ የደከመውን አዕምሮ በበዓሉ መነሻ የሚያሳርፉበት፣ በአዲስ መንፈስ ለቀጣዩ ዓመት ሥራ የሚዘጋጁበትና የህይወታቸው መለወጫና ማደሻ አድርገው የሚቆጥሩት ብቻ ሳይሆን ተፈጥሮም አካባቢዉን በአዲስ አበባ በማጋጌጥ የተፈጥሮ ተሀድሶ ጭምር የሚካሄድበት ነዉ። በተጨማሪም ሰው ብቻ ሳይሆን እንስሳትም ጭምር የማይመቸውን የክረምቱን ጭጋግ፣ጨለማንና ብርዱን አልፈው ፀሐይን በማግኘት የሚደሰቱበት በክረምት ይነድፋቸው ከነበረ ትንኝ  አርፈው በነጻነት ሳር የሚግጡበት ነው ይላሉ፡፡ ስለዚህ ያሆዴ ማለት መሻገር ማለት ሲሆን ከአሮጌዉ ዓመት ወደ አድሱ ዓመት ከጥላቻ ወደ እርቅ ከመጥፎ ወደ ጥሩ ነገር  መሻገርን የሚያመላክት ቃል ነው፡፡ 

የሃዲያ ብሄር የዘመን መለወጫ በዓሉ ዝግጅት በተመለከተ ከነሐሴ አጋመሽ ጀምሮ እሰከ በዓሉ ዋዜማ ድረስ ሁሉም የቤተሰብ አባላት ዝግጅት ያደርጋሉ፡፡ የያሆዴ በዓል ዋዜማ በመስከረም 13 ሴቶች ተሰብስበው የአተካና ቆጮ በሚያዘጋጁበት ቀን ዊላዊሎ/Willaawilloo/ በመብላት ይጀመራል። ቀጥሎም በ14 ማታ ፉሊታ/Fulitta/ብለው በሚጠሩት ቀን ጦምቦራ/Xomborraa/ተለኩሶ አተካና በመብላት ይከበራል። በዚህም ምሽት የፉሊታ ልጀች ወላጆችን የመባረክ ስርዓት ይካሄደል። አባት እና እናት አምና ለልጀች የገቡትን ስዕለት/ቃል ይፈጽማሉ ለቀጠዩ ዓመት ደግሞ ሌላ ቃል ይገባሉ።

በዋናነት በመስከረም 15/16 በዕርድ ቀን ላይ የሚካሄደዉ የአከባበር ሥነ-ሥርዓት ክንዋኔ በብሔሩ አንጋፋ የባህል ሽማግሌዋች ምርቃት ነዉ። ይህም የምርቃቱ ስርአት ስለ አካባቢዉ ህዝብ፣ ስለ መንግስት፣ ስለ ሀገር ሠላም መልካምን በመመኘት ሽማግሌዋች ተስማምተዉ የተናገሩት ቃል እንደሚሆን በማመን እንድህ ይላሉ:- በሀገራችን ሰላም ይወረድልን ልማት ብልጽግን ይሁንልን፣በሽታ ከሀገራችን ይጥፋ፣ የወለዱት ይፋፋ፣ርሀብ ይወገድልን፣ ለሀገር እና ለህዝብ እድገት አሳቢ መንግስት ያኑርልን፣ እያሉ እየተቀባበሉ ይመርቃሉ።

በሼማታዉ/በቱታ አሰተባባሪነት የእርድ በሬ ወጥቶ በአከባቢዉ ታዋቂ ሽማግሌ ደጃፍ /ሀዲይ ነፈራ ላይ ይቆማል በዘህም እማወረዋ ያዘጋጀችዉን ለጋ ቅቤ፣ የገብስ ቡሎ፣ አተካና  እና ቦርዴ ከሣር ጋር ይዛ ትቀረባለች ሽማግሌዎችም ተቀብለዋት በሰርዶ ሳር በበሬዉ ሻኛ ላይ ቅቤ ይቀባሉ፤ መጠጡንም ወስዶ ከሻኛዉ ወደ ጅራቱ ይደፉታል። በዚህም ህደት ሽማግሌዋች እንድህ ይላሉ ክፉ ቀን አይምጣ፣ረሀብ ችግር ይልቀቀን፣ጥጋብ ይስፈን ፣ልጅ ይቦርቅ፣ ጥጃ ይፈንጭ፣ሀገር ሰላም ይሁን በማለት ፀሎት/ፋቴ/ጋቢማ ከፈጸሙ በኃላ በሬዉ ይጣላል።ሌላዉ በዚህ ስርአት የማይቀር ነገር ቢኖር ሰንገዉ ለታረደበት ቤት አባወራ የሚሰጥ የስጋ ሰጦታ ነዉ ይህም አባወራዉ ሙሉ ሻኛ ከመከፋፈሉ አስቀድሞ በእጁ መዳፍ ጨብጦ እንድይዝ ይደረግና በጭብጡ ልክ ተቆረጦ ይሰጠወል። በቤት ዉስጥ የወለደች አራስ ወይም ግርዘኛ ካለ የሹልዳ ስጋ ይሰጠዋል።

 ሥጋዉም በባለሙያ ተበልቶ ካለቀ በኃላ የቱታዉ አስተባባር ከሚየስፈልገዉ የስጋ ዓይነት ሁሉ አውጥቶ በመስጠት አርዛ/ጎረድ ጎረድ እንድዘጋጅ ይሰጣል። ተበልቶ የተዘጋጀዉ ሥጋ በቱታዉ/በሼማተዉ ቁጥር እንድከፋፈል ተደርጎ በኮባ ቅጠል ይቀመጣል። ቱታዉም ዕጣዉን እያነሣ  ሥጋውን እንዲቀበል ይደረጋል። አንደአንድ አከባቢ ላይ ስጋዉ በተረደዉ ቀን ሲከፋፈሉ አብዛኛዉ አከባቢ በማግስቱ ስጋዉን ይዞ ይሔዳል፡፡ ከዚህም በኃላ የተዘጋጀዉ አርዛ ከቆጮ ቂጣ እና ከናቃሮ ጋር በጋራ ይመገባሉ። በመጨረሻም ተመራርቀዉ ወደ የቤታቸዉ በመሄድ ከቤተሰቦቻቸዉ ጋር ወሩ እስኪያልቅ የተከመቸዉን ምግብ በመብላት ያሳልፋሉ።

 

በሀድያ ብሄር በያሆዴ ዘመን መለወጫ በዓል በጣም ትኩረት ከሚሰጣቸው የምግብ ዓይነቶች ከእንሰት፣ከገብስ እና ከእንስሳት ውጤቶች የሚዘጋጁ ዋና ዋናዎቹ ናቸው። እነዚህም ቆጮ፣ቡላ፣አተካና፤አይብ፣ቡሎ፣ዊላዊሎ፣ሱልሶኦናቸው። 

 

 

 

 

 

 

 

 

በሀዲያ ብሄር ዘመን መለወጫ ያሆዴ በዓል ላይ የሚቀርቡ  

የዘፈን/ጫዋታ ዓይነቶች ከበዓሉ ቀደም ብሎ በፉሊታ ቀን ማታ ጦምቦራ/ችቦ አቀጣጥለው ሆሌኤ ጨዋታ ይጫወታሉ፡፡ የዚህም  ሂደት ባለፈው ዓመት የነበርክ ክፉ በሽታና ችጋር ውጣ እያሉ በተግባር  የችቦ እሳት ለኩሰው እንዲህ እየዘፈኑና እየተጫወቱ ያባርራሉ።