Skip to main content

የከምባታ ዞን ባህላዊ መስህብ

የከምባታ ዞን ባህላዊ መስህብ 

የከምባታ ብሄረሰብ ባህላዊ የዕርቅና የፍትህ ሥነ-ሥርዓት

Image removed.

የከምባታ ብሄረሰብ ባህላዊ መተዳደሪያ ደንብ ከምባቲ ሴረ (Kambaati seera) በመባል ይታወቃል።የከምባታ ሴራ በቀደምቶቹ የከምባታ አባቶች የተመሰረተ ያልተፃፈ ህገ-ደንብ ስሆን በየዘመናቱ እንደየሁኔታው እየተሻሻለ የማህበረሰቡን ቋንቋ ወግና ታሪክ ጠብቆ የህዝብን ማህበራዊ ኢኮኖሚያዊና ባህላዊ መሠረቱን ባገናዘበ ሁኔታ ተግባራዊ እየሆነ እስከአሁን የቆየ የህዝብ የህግና የፍትህ ዕሴቱ ነው።

 የከምባታ ብሄረሰብ ባህላዊ ህገ-ደንብ የሽማግሌዎች ደንብ(ሴራ) የሠርግ ደንብ የለቅሶ ደንብ የቅድመ-ወሊድና  ድህረ-ወሊድ ደንብ የመስቀል በዓል ደንብ የጋራ መሬቶች አስተዳደር ደንብ የድንባር ደንብ... ወዘተ እየተባለ የአኗኗር ስርዓቱ በባህላዊ ህግና ሥርዓት የታጠረ ቢሆንም በዋናነት አጠቃላይ የዳኝነትና የፍትህ ተቋማት በ4 ይካፈላሉ።

  •  የኮካታ ህገ-ደንብ (ኮካቲ ሴረ) የሁሉም 

 ከምባታ  የጋራ ም/ቤት ስሆን ትልቁ የስልጣን ባለቤት በመሆን ትልልቅ የፖለቲካ ማህበራዊ ኤኮኖሚያዊ እንዲሁም የህግና የፍትህ ውሳኔዎችን ያስተላልፋል።

  • የአስተዳደር ክልል ህገ-ደንብ (ጎቺ ሴረ) 

የከምባታ ባህላዊ አስተዳደር ሀምበርቾ ተራራን ማዕከል አድሮጎ በ30 ክልሎች የተከፋፈለ በመሆኑ እያንዳንዳቸው እንደየአካባቢው ተጨባጭ ሁኔታ የሚተዳደሩበት ደንብ ነው።

  • የዕድር ህገ-ደንብ (ሄረ ሴረ)  በእያንዳንዱ አስተዳደር ክልል ውስጥ በርከት ያሉ ትዳር የመሠረቱ ነዋሪዎች በማህበራዊ ኑሮአቸው የሚያጋጥሙ የሀዘንና ደስታ ጉዳዮችን በጋራ የሚወጡበት ባህላዊ ሥርዓት ነው።

  • የጎሳ ህገ-ደንብ (ቦኪ ሴረ) እያንዳንዱ ጎሳ ታላላቆቹን በመምረጥ በራሱ ጎሳ አባላትም ሆነ ከሌሎች ጋር የሚፈጠሩ ግጭቶችን እየፈታ በሰላም የሚኖርበት ባህላዊ ደንብ ነው።

  • ሁሉም ደንቦች እርስ በርሳቸው የማይጣረሱ ሆነው ተቋማቱም በየደረጃቸውና በተሰጣቸው ሥልጣን መሠረት ከከባድ እስከ ቀላል ግጭቶችን አብዛኛውን ጊዜ በበዳይ አካል አስተናጋጅነት በበራፉ ባለው ዛፍ ጥላ ሥር ባለው ለምለም ሣር ላይ (ሀሌቾን ሀሩፋን) በመሰብሰብ ተበዳዮች እንዲካሱ በዳዮች ተገቢውን ቅጣትና ተግሳፅ እንዲያገኙ ይደረጋል። በዳኝነት ወቅት በዳይ ጥፋተኝነቱን ባለማመን ቀጠሮ የሚበዛ ስሆን በተደጋጋሚ አስገዳጅ መስተንግዶ  ወጪ የኢኮኖሚ ጉዳት ወይም መድቀቅ ይደርስበታል። ይህም ''ቡተኡ'' በመባል ይታወቃል።  የግድያና ሌላ  ከበድ ያለ ጥፋት ያደረሰ ሰው የካሳ ገንዘብ ሲጠየቅ የጎሳው አባላት በሙሉ በመሰብሰብ የሚከፍሉት ገንዘብ'' ወዝኑተ'' ይባላል። የከምባታ ብሄረሰብ ባህላዊ አስተዳደር የዳኝነትና የፍትህ ሥርዓት ለረዥም ዘመን በህዝቦች መካካል የሚፈጠሩ ግጭቶችን እየፈታ የቆየ ለዘመናዊ የፍትህ ሥርዓትም አጋዥ በመሆኑ ተጠብቆ ለቀጣዩ ትውለድ መሻገር ይኖርበታል። 

 ከምባታ ስለ ባህላዊ ሴራው እንዲህ ስል ይገልጻል 

 

"መቃሙ ቆጠረሃ"        /ሀይለኛ ብርቱውን/

"መቄቤሉ ላፈሃ"      /አቅም የሌለውን ደካማውን/

"መንተለለ ቀሉሃ"    /ፈፅሞ ቅል የሆነውን/"ሜጡ አስ ገሽኖ ሴረ መኒ ሮስሼሃ ከምባቱ"

"ሞንቹ ሀገፈሃ"        /ሞኝ ከረፈፉን/ "ምጤቹ ሉባሙሃ"     /አስተዋይ ሙያተኛውን/ መሌሰ ሀዮኣሙሃ"    /ጥበብ ግርማ ሞገስ ያለውን/

 

                                           መሳላ ፦የከምባታ ዘመን መለወጫ

 

Image removed.በመሳላ ዕለት በአጋጣሚ ሰዉ ብሞት እንኳን የማይለቀስ ስሆን የለቅሶ ሥነ- ሥርዓቱ በቀጣዮቹ ቀናት ይሆናል፡፡ መሳላ የመረዳዳት፣ የመተሳሰብና የመደጋጋፍ በዓል ነዉ፡፡አባቶች/ሼማታ/ የመሳላን ሰንጋ በጋራ ይገዛሉ ፣ ወጣቶች የመሳላን የማገዶ እንጨት በጋራ ይፈልጣሉ፣ደመራዉን በጋራ ይደምራሉ፣ እናቶች የመሳላን የቆጮ እንሰት በጋራ ይፊቃሉ፣ የቅቤና የወተት ቁጠባ/ዊጆ/ በጋራ ይገባሉ፣ሽማግሌ የተጣለዉን በጋራ ያስታርቃል፣ልጆች /እረኞች/ ከብቶችን አስቀድሞ ተከልሎ በተዘጋጀ የጋራ ቦታ/ቦቆታ/ በጋራ ያሰማራሉ፣ የኮንዴቾ/የስንደዶ አምባር በጋራ ሰርተዉ በጋራ ይጨወታሉ፣ልጃገረዶች የቤት መገልገያ መሣሪያ የሚሰሩበትን ስንደዶ በጋራ ይለቅማሉ፡፡መሳላ የማዝናኛ ፣የንፅህናና የታሃድሶ በዓል ነዉ፡፡የተገረዙ ወጣቶች  የትግል/ገምሻ/ ይጨወታሉ ፣ ሁሉም ሰዉ ግፋታ ይጨወታል፣በግፋታ የሴቶች ሙያ ይወደሳል ፣ሀገሩን ከጠላት ለመከላከል የዘመተዉ፣ በእርሻዉ ሥራ  ጎበዝ የሆነዉ ፣በህዝብ  አስተዳደር አድናቆን ያተተረፈዉ ሁሉ በግፋታ ይሞገሳል፡፡ በመሳላ ማግስት ወጣት ወንዶች የሴቶችን ቀሚስ በመልበስ በየመንደሩ እየዞሩ የመሳላን ባህላዊ ምግብ እየበሉና ባህላዊ መጠጥ እየጠጡ የሴቶችን ሙያ እያወደሱና እያደነቁ / ባሊ ሄሌሌ/ እያሉ ይጨፍራሉ፡፡ ያገቡ ወንድና ሴት ልጆች ለወላጆቻቸዉ የተለያዩ ባህላዊ ምግቦችንና መጠጦችን  አልባሳትና ሌሎች ስጦታዎችን ከወቅቱ አዳይ አባባ ጋር በስጦታ በማበርከት ምርቃት ይቀበላሉ ። ይህ ባህላዊ የስጦታ አሰጣጥ ሥርዓት የአባባ/ዘራሮ ሴራ/  ይባላል፡፡በ    መሳላ ሰዎች ብቻ ሳይሆኑ እንስሳትም ጭምር የሚደሰቱበት ባዓል ነዉ፡፡ በመሳላ እንኳን ሰዉ እንስሳትም አይራቡም ፡፡ ለዚህም ነዉ Anniintas yoo qoqo masaali bari duubano yeenoo/ ፡፡  ‹‹ ከባለቤቱ የከረመ ጎሮሮ በመሳላ እለት ይጠግባል!››የሚባለዉ ፡፡ በመሳላ ለተቸገረ ሰዉ ብድር ጠይቆ አይከለከልም፡፡ ለሌለዉ ሳይጠይቅም ይሰጠዋል፡፡ ሰንጋ ያደለበ ሰዉ በዱቤ/ኣበ/ ይሸጣል፡፡ እናቶች የአተካኖ ቆጮ ቅቤና ወተት ለሌላቸዉ ያካፍላሉ፡፡መሳላ ለከምባታ ብሄር በየዓመቱ የታሪክ አሻራንም እየጣለ የሚያልፍ ባህላዊ ክብረ- በዓል ሲሆን በየአመቱ መስከራም አንድ /ሌንጃ/ እለት ልጆች የበዓሉን በረከት እፈሱ /ሆሌ ሆሌ/ እያሉ እየጨፈሩ ለምለም የእንግጫ  ሳር ለቅመዉ በማምጣት በወላጆቻቸዉ ጉልበት ላይበማስቀመጥ ምርቃት ይቀበላሉ፡ ፡አባቶች  ለምለሙን ሣር በሶስትዮሽ ገመድ ሰርተዉ በቤቱ መሶሶ ላይ ያስራሉ ፡፡በዚህም የሰዎችንና የእንስሳትን ዕድሜ ይቆጥሩበታል፡፡ ስንት መሳላ በለህ ? ተብሎ እንጂ ዕድሜህ ስንት ነዉ? ተብሎ አይጠየቅም፡፡ የመንግሥታትና የመሪዎች ለዉጥ እንዲሁም የተለያዩ ትልልቅ ክስተቶች ዘመን የሚታወቀዉ ይህንነ በመሶሶ ላይ የታሰረዉን ገመድ በመቁጠር ነዉ፡፡  መሳላ በርካታ ለመህበረሰቡ ጠቃሚ ዕሴቶችን ሰብስቦ የያዘ በዓል በመሆኑ በቅርብ ዓመታት በተጀመረዉ መልኩ በየዓመቱ ወቅቱን ጠብቆ በአደባባይ መከበሩን ይቀጥላል፡፡ መሳለና በዉስጡ ያሉት በርካታ ጠቃሚ ዕሴቶች ለማህበራዊ ለእኮኖሚያዊና ለፖሊትካዊ ዕድገት ያለዉ ዕምቅ አቅም  የጎለ በመሆኑ በዓለም -አቀፉ የሳይንስ የትምህርትና የባህል ድርጅት /UNESCO/ እንዲመዘገብ የቅድመ- ዝግጅት ሥራዎች እየተሰሩ ይገኛሉ፡፡ በቀጣይም መሳላ ባህላዊ  የአከባባር ሥርዓቱን ጠብቆ በህዝቡ ባለቤትነት በአደባባይ እየተከበረ የዓለም ቅርስ እንዲሆን የሁሉም የህብረተሰብ ርብርብ ያስፈልገዋል።