የጉራጌ ዞን ባህላዊ መስህቦች
የጉራጌ ዞን ባህላዊ መስህቦች
መስቀል በጉራጌ

የመስቀል በዓል በጉራጌ ብሄረሰብ አጀማመረሩ እና ባህላዊ ትውፊት ምድረ ጉራጌ ቅዱሳን በኪደተ እግራቸው የባረኩትና የክርስትናውም ትምህርት ከተአምራት ጋርአስተባብረው የሰበኩበት ታላቅና ታሪካዊ ቦታ ነው። መዛግብት እንደሚያስረዱን ከ13ኛው ክፍለ ዘመን ጀምሮ የሆነ የክርስትና ጉዞን እናገኝበታለን። ምድረ ከብድ አቡነ ገብረ መንፈስ ቅዱስ ገዳም ምሁር ኢየሱስ ገዳም ኤነር አማኑኤል ገዳም አትርፎ ጊዮርጊስ በተጠቀሰው ዕድሜ ከተተከሉት ጥንታዊያን አብያተ ክርስቲያናት መካከል ተጠቃሾች ናቸዉ።ለጊዜው ታሪኩን ገታ አድርገን መስቀል በጉራጌ እንዴት እንደተጀመረ እንይ።ከጻድቁ አባታችን ከአቡነ ገብረ መንፈስ ቅዱስ በኋላ የጉራጌን ምድር ያስተማሩ ጻድቁ አባታችን አቡነ ዜና ማርቆስ በብሩህ ደመና ተጭኖ ጉራጌ ሃገር እንደደረሰ ገደላቸው ይናገራል። አቡነ-ዜናማርቆስ ስብከታቸው ከምሁር ጀምረው እየሰበኩ ባሉበት ወቅት ነበር ወደ ሐገር ገዢው ወደ መኮነኑ ቤት ቀርበው በጌታ በኢየሱስ ክርስቶስ ስም እርቦኛል አብላኝ ብለው ንጉሱን ለመኑት ንጉሱንም ይህን የምትጠራው ጌታ የምትለው ማነው ? እኛ አምላካችን ማኮስ ነው ከእሱሌላ ጌታ አናውቅም አለ:: አባታችን ዜናማርቆስም እርሱም ሰማይና ምድር የፈጠረ አለምን ሁሉ የሚገዛ ሁሉ በእርሱ የሆነ የእኔና የአንተ አምላክ አለው::እስቲ ያንተአምላክ አሳየኝ እኔም አሰግድለት ዘንድ ወደእርሱ እንሂድ አለው :: ወደስፍራው በደረሱ ጊዜ አባታችንም በስመአብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ ስም አማትበው ቢገስፁት ሙሴ እብራዊዉን በአዋሻ እንደቀበረው ጣኦቱ መሬት ተከፍቶ ዋጠችው :: ንጉሱም ተቆጣ አባታችንን ያሰቃየው ጀመር ሊገለውም ጦሩን ሰበቀ በዚያን ጊዜ አምላኩ ማኮስ የዋጠችው መሬት ተሰንጥቃ ከነሰራዊቱ እሱንም ዋጠችው:: በዛን ሰአት የነበሩ ሰዎች ስለ እራሳቸውም እጅግ ፈሩ አባት ሆይ በአምላክህ አመንን አመንን አመንን በአምላክህ ስም አጥምቀን አሉት እርሱም በደመና ተነጥቆ እስክንድርያ ደርሶ ከአባ ብንያም ቅስና ተቀብሎ ወደ ምሁር ተመልሶ እነዚያን ሰዎች አስተምሮ አጥምቋቸዋል። 12900 ሰዎች ክርስትና ተቀበሉ አባታችን ወንጌል እያስተማረ በነበሩበት ጊዜ ወላጆች ሁሉ በጉባኤው ላይ ሳሉ ቀኑ መሽቶ ነበረና ልጆች ስንደዶ(ጦት) አብርተው ፍለጋ ወጡ ወላጆችም ይህ እሳት የልጆች እሳት ነው ልጆች ናቸዉ አሉ።ያን የያዙት እሳት ሰብስበው አንድ ላይ ስብስበው አቃጠሉት ቀኑም መስከረም 14 ነበረና በእያንዳንዱ ደጅ መስከረም 14 የሚበራውን የልጆች ደመራ ተጀመረ።አባታችን ዜና ማርቆስ ከአባ ቄርሎስ ጋር ሆነው በደመና ተነጥቀው ወደ ምሁር ደረሱ ጼዋ መስቀል በቤቷ ተቀበላቻቸው እርሷም የአውጊት ሚስት ናት በሚያስተምሩበት ወቅት አንድ ሰው ስለ ትንሳኤ ሙታን ጥያቄ ጠየቀ አባታችንም ስለ ትንሳኤ ሙታን ካስተማረ በኋላ ከ 5 ዓመት በፊት ሞቶ የነበረውን መኮንን አውጊትን ከሞት አስነሳላቸው።በዚህ ጊዜ ባለቤቱ ጼዋ መስቀል ከልጆቹ ጋር እየጮኸች እልል አለች የሃገሩም ሰዎች ሁሉ ይህንን ሰሙ።ወቅቱም መስከረም 15 ነበር ሁላቸውም ለእርድ የሚሆን በየቤታቸው አቀረቡ አባታችን አቡነዜናማርቆስም እንዲ አሉ ዛሬ የደስታ ቀነው ሰዉ እንስሳውንም ሁሉም ደስ ሊለው ይገባልንጉሱም እንዲህአለ~ እኔ በመስቀል በሞት ተገፍቼ ከተለየሗቸው ቤተሰቦቼ ዛሬ ተገናኝቻለሁ ማንም ከቤተሰቡ ተለይቶ አይዋል ከዚያ ጊዜ አንስቶ በደማቅ ሁኔታ መከበር ተጀመረ የሃገሬው ተወላጅ የሆነ ሁሉ ከያለበት ወደ ሃገር ቤት እየገባ ማክበር ተጀመረ ።
የአረፋ በዓል በጉራጌ ዞን

በጉራጌ ዞን ከሚከበሩት ኃይማኖታዊ ክብረ-በዓላት መሃከል የአረፋ በዓል አንዱ ነው፡፡ ይህ በዓል የእስልምና ኃይማኖት ተከታይ በሆኑት የብሔሩ ተወላጆች ዘንድ ከፍተኛ ግምት ተሰጥቶት ደምቆ ይከበራል፡፡ ለአረፋ በዓል የሚደረገው ዝግጅት በዓሉ ከመድረሱ ቀደም ብለው ባሉት ወራቶች ውስጥ የሚጠናቀቅ ይሆናል፡፡ በዚህም እናቶች ለበዓሉ የሚሆን መጪ(ምርጥ) ቆጮ፣ቅቤ፣ሚጥሚጣ ...ወዘተ ሲያዘጋጁ ሴቶች ልጆቻቸው ደግሞ የመኖሪያ ቤቶች በማስዋብ፣የመመገቢያ ቁሶችን በማጽዳትናሎች ለበዓሉ የሚያስፈልጉቅድመሰናዶዎችን በማሟላት ስራ ይጠመዳሉ፡፡ ልክ እንደ ሴቶቹ ሁሉ ወንዶቹም ለአረፋ በዓል የሚያከናውኗቸው የስራ ድርሻ አላቸው፡፡ ለማገዶ የሚሆን እንጨት ፈልጦ ማዘጋጀት፣ለእርድ የሚሆን ከብት ማቅረብ በአባቶችና በወንድ ልጆቻቸው የሚከወን ይሆናል፡፡
አረፋ የእስልምና እምነት ተከታይ የሆነውየጉራጌ ብሄር ተወላጅ በተለያዩ ስራዎች ላይ ተሰማርቶ ከየሚኖርበት የተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች ወደ የትውልድ ቀዬው የሚመለስበትና በዓሉን ከወላጆች፣ ቤተሰብ፣ዘመድ አዝማድ ከአብሮ አደግ ጓደኛ...ወዘተ ጋር በመሆን የሚያከብርበት ታላቅ በዓል እንደሆነ ይታወቃል፡፡ በመሀኑም የአረፋ በዓል በስራ ምክንያት ተራርቆ የቆየውንም ሙስሊም የዞኑ ተወላጅ ከያለበት አሰባስቦ የሚያገናኝም በዓል ነው ለማለት ይቻላል፡፡ ከዚህ በተጨማሪ የአረፋ በዓል ቀደም ሲል ተጫጭተው የቆዩ የሚሞሸሩበት፣ሌሎች ደግሞ በቀጣዩ ሶስት ጉልቻ ለመመስረት የትዳር ጓደኛቸውን የሚመርጡበትና በባህሉ መሰረት የሚያጩበትም ጭምር መሆኑን የብሔረሰቡ ተወላጆች ያስረዳሉ፡፡ ሌላው የአረፋ በዓል ያለው ማህበራዊ ፋይዳ በተጣሉ ሰዎች መሀል እርቀ - ሰላም እንዲወርድ የማስቻል ብቃቱ ይሆናል፡፡ ከበዓሉ በፊት የተቀያየሙ ባልና ሚስት፣ልጅና ወላጅ፣ጎረቤታሞች ...ወዘተ በአረፋ ሰሞን "ይቅር" ተባብለው ሰላምን ያወርዳሉ፡፡ ለበዓሉ የተዘጋጀውን አብረው በመብላትና በመጠጣት ይደሰታሉም፡፡ የአረፋ በዓል ሌላው ማህበራዊው ፋይዳው ከአራቱም ማዕዘናት በዓሉን ለማክበር ወደ ትውልድ አካባቢው የመጣው ሙስሊሙ የዞኑ ተወላጅ በቤተሰባዊና ማህበራዊ ጉዳዮች ላይ መክሮ ለተለያዩ ችግሮች መፍትሔዎችን የሚሻበት መሆኑ ይሆናል፡፡ የቤተሰብ ህይወት እንዲሻሻል "ምን ይደረግ?" በአካባቢው ልማት እንዲስፋፋ "ምን እንስራ?" ብለው ለበዓሉእትብታቸው ወደ ተቀበረበት ምድር የተመለሱት በአንድነት ከቤተሰብ እና ከማህበረሰቡ ጋር ይመክራሉ፡፡ መፍትሔዎችንም ያበጃሉ፡፡ ባጠቃላይ የአረፋ በዓል ሙስሊም በሆነው የዞኑ ተወላጅ ዘንድ ሁሉ ከፍተኛ ግምት ሰጥቶት የሚከበር በዓል ሲሆን ከመብላትና መጠጣቱ ባሻገር ሌሎች ብዛት ያላቸው ቤተሰባዊና ማህበራዊ ፋይዳዎችም ጭምር ያሉት እንደሆነ ይታወቃል፡፡
ኩርፍወ
የጉራጌ ብሔር እንደሌሎቹ የሀገራችን ብሔር ብሔረሰቦች ሁሉ የሚታወቅባቸው አያሌ ባህላዊ ክንዋኔዎች አሉት፡፡ ከእነዚህ ቀን ተቆርጦላቸው ፣የመከወኛ ቦታ ተወስኖላቸው የየራሳቸው መገለጫ የሆኑ አልባሳትና ቁሶች ተዘጋጅተውላቸው ስንኝ እየተቋጠረ ከሚዜምላቸውና ዳንኪራ ከሚረገጥላቸው ባህላዊ ክዋኔዎች አንዱ ኩርፍወ ነው፡፡ኩርፍወ በጉራጌ ብሔር ዘንድ በየዓመቱ በሰሙነ ህማማት ተጀምሮ በልጃገረዶች እስከ ዳግም ትንሳኤ ድረስ ባሉት ቀናቶች እየተዘፈነ የሚቆይ ባህላዊ የጨዋታ ዓይነት ነው፡፡ ይህ ትውፊታዊ ክዋኔ መች እንደተጀመረ በውል የሚያሳዩን የፅሁፍ መረጃዎች ባይኖሩንም ከእድሜ ጠገቦቹ የብሔሩ ተወላጆች አንደበት ያገኘነው ማስረጃ ኩርፍወ ከአያሌ ዓመታት በፊት በብሔሩ ውስጥ ይከወኑ ከነበሩት አዝናኝና ማራኪ ባህላዊ ጭፈራዎች መሃከል አንዱና አንጋፋው መሆኑን ይነግሩናል፡፡የኩርፍወ ጨዋታተሳታፊዎችልጃገረዶች ብቻ ሲሆኑ በየዓመቱ በሰሙነ ህማማት እነዚሁ ልጃገረዶች አምባሬ የሚባል ተክል ቅጠል ከስሩ ይነቅሉና ሸንሽነውና አስጊጠውት ወገባቸው ላይ አስረው አበባውን ደግሞ በእጃቸው ይዘው እያወዛወዙ እያዜሙ ይጨፍራሉ፡፡የኩርፍወ ጨዋታ መከወኛ ስፍራ የለመለመ መስክ ወይም ሰፋፊ ጀፎሮ በሚገኝበት አካባባቢ ሲሆን ልጃገረዶች ከየቤታቸው ሲወጡ ተጋጊጠውና አምረው ደምቀው መታየታቸው ግድ ስለሆነ ሁላቸውም ባህላዊ የክት ልብሳቸውን ለብሰው በአምባርና በአልቦ ተሽቆጥቁጠው ፀጉራቸውን ሹርባ ተሰርተው ከየአቅጣጫው ወደዚሁ ስፍራ ይተማሉ ዓመታዊ ልምዳቸውን ከእድሜ አቻዎቻቸው ጋር ሆነው በዜማና በዳንኪራ ይወጣሉ፡፡
ግቻሜ
በጉራጌ ብሔር ዘንድ ህዝባዊ ከሆኑ ባህላዊ ጨዋታዎች መሃል አንዱ ጊቻሜ ነው፡፡ይህ ባህላዊ ጨዋታ በሴቶች ብቻ የሚዜም ሲሆን ትርጓሜውም ‹‹ነይ ግጠሚኝ-እንፎካከር››የሚል እንደሆነ ይነገራል፡፡ በየወሩ የማርያም ዕለት ተገናኝተው ፅዋ በሚቃመሱ ማህበርተኞች የሚዘወተረው ጊቻሜ ልክ እንደቃሉ ትርጓሜ ሁሉ በእናቶች መሃል ‹‹ እኔ እበልጥ እኔ እበልጥ›› እየተባለ ባልትና፣ ቁንጅናን፣ ቤተሰብን፣ ዘመድን…ወዘተ በማንሳት አንዷ የእርሷን አስበልጣ የሌላኛውን አሳንሳ የምትናገርበት ዘፍንና ዳንኪራ ነው፡፡ ጊቻሜ የሚዜምበት ስፍራ በቤተ-ክርስቲያን አካባቢ ነበረ፡፡ በየዓመቱ ጥር 21 ቀን በሚውለው የማርያም ንግስ በዓል ላይ እናቶች ግቻሜን ይዘፍናሉ፡፡ይጨፍራሉም፡፡ በየዓመቱ የአስተርዮ ማርያም ንግስ ላይ እናቶች ታቦቱን አጅበው ዳንኪራ እየረገጡ ጊቻሜን ያዜማሉ‹ኤቦ ንገሽ! ማርያም ንገሽ!››እያሉ ስዕለታቸውን እያደረሱ ልባዊ ደስታቸውን በጊቻሜ ይገልፃሉ፡፡ በተጨማሪም ጊቻሜ በሠርግ ቦታዎችም ሲከወን ይታያል፡፡
ባህላዊ ቤት
የጉራጌ ቤት ሶስት ደረጃ አለው፡፡ ጓየ፣ኸራርና ዘገር በሚል ይለያል፡፡ ጓየ/ዋና ቤት/ ስፋቱ 50 ጫማ በ50 ጫማ ሆኖ አባወራውና እማወራዋ የሚውሉበት፣የሚያድሩበትና በየዕለቱ በግቢ ውስጥ የሚሰሩ ሰራተኞችና ጎረቤቶች የሚስተናገዱበት ወይም የሚታደሙበት ሲሆን ኸራር/እልፍኝ ስፋቱ 36 ጫማ በ36 ጫማ ሆኖ አጊጦና ተውቦ ሰርክ አገልግሎት የሚሰጥ ሳይሆን አብዛኛውን ጊዜ ለእንግዶች መቀበያነትና የደረሱ ወጣት ተማሪዎች ወይም ከተለያየ ከተማ በተለያዩ ምክንያቶችና ለበዓላት የሚመጡ ቤተሰቦች ማረፊያነት የሚያገለግል ነው፡፡ ትንሹና ዘገር/ማድቤት ወይም ጪስ ቤት/ የሚባለው ስፋቱ 15 ጫማ በ15 ጫማ ሆኖ የየዕለቱ ምግብ የሚዘጋጅበትና የሚበስልበት ነው፡፡ ስለቤቶቹ ደረጃና አገልግሎታቸው ይህን ያህል ካልን ስለ አሰራራቸው ጥቂት ነገር ለማለት እንሞክራለን፡፡

ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ እሴቶች
የጉራጌ ብሔር በአብነት ሊጠቀሱ የሚችሉ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ፋይዳ ያላቸው እሴቶች ለኢትዮጵያ ብሔር/ብሔረሰቦችና ህዝቦች ማበርከታቸው ይታወቃል፡፡ ጉራጌ በማህበራዊ ህይወቱ ከሌሎች የኢትዮጵያ ብሔር/ብሔረሰቦችና ህዝቦች ጋር ተፈቃቅሮና ተከባብሮ አብሮ በመኖር ባህሉ፣እንዲሁም በስራ ፈጣሪነቱና ወዳድነቱ፣በጋራ እንደግ መንፈስ መረዳዳቱና መተሳሰቡ፣በፍቅሩና በሰላም ተምሳሌትነቱ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ፋይዳቸው በኢትዮጵያ ህዝቦች ማህበራዊ ህይወት ውስጥ ትልቅ ስፍራ ይዘው ዛሬን ድረስ የዘለቁና በሂደት እያደጉ ከመጡ እሴቶች የተወሰኑትን ለመዳሰስ እንሞክራለን፡፡
ውጆ/ዳማዳ/ የቅቤ ወይም የወተት እቁብ/
በጉራጌ ብሔር በአንድ መንደር የሚኖሩ አርሶ አደር እናቶች ከየቤታቸው የቅቤ ዳማዳ/እቁብ/ በመሰብሰብ እያንዳንዷ እናት በተራ እንድትወስድ የሚደረግበት ማህበራዊ ስርዓት ውጆ በመባል ይታወቃል፡፡ በአንዳንድ ቤተ-ጉራጌ እናቶች ዘንድ የሚሰበሰበው ውጆ ቅቤ መሆኑ ቀርቶ በወተት የሚተካበት አሰራርም አለ በተለይም አንዲት እናት ከላሞቿ የምታገኘው የወተት መጠን አነስተኛ ሲሆንባትና ራሱን አስችላ አጠራቅማ እንዳትንጠው መጠኑ ስለሚያንስባትና ለተፈለገው ጉዳይ ሊውልላት ስለማይችል ከብዙ የውጆ አባላት የሚጠራቀመው ወተት ለባለተረኛዋ ይሰጥና ንጣ አይብና ቅቤ በማውጣት ለችግሯ ለበዓልና ለተለያዩ ማህበራዊ ጉዳዮች ታውለዋለች፡፡
ይህ ዓይነቱ የውጆ አሰባሰብ በጉራጌ እናቶች ህይወት ትልቅ መስተጋብርና ማህበራዊ ትስስር የፈጠረ ሲሆን እሴቱ እያደገ ሄዶ በአገር ቤት ገበያ በንግድ እንቅስቃሴ ውስት ሲሳተፉ የነበሩ እናቶች የገንዘብ አቅማቸውን ለማጎልበት በማሰብ የገንዘብ እቁብም እንደጀመሩ የብሔሩ አንጋፎች ይናገራሉ፡፡
እቁብ የቀርሺ/ብር/ ደማዳ
ከዘመናት በፊት በአገር ቤት በተለያዩ አካባቢዎች ይኖሩ በነበሩት የጉራጌ እናቶች ተጀምሮ የነበረው የቅቤ/የወተት ውጆ/ደማዳ/ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ፋይዳው ጎልብቶና አድጎ በቤት ውስጥ አገልግሎቶች ሳይወሰን በመስክ ስራ ስንኳ የተሰማሩ የነጋዴዎችን አቅም ለማጎልበት እንዲያስችል ወደ ብር እቁብነት መሸጋገሩ ይታወቃል፡፡
በአገር ቤት ከገበያ ገበያ በመዟዟር ሲደረግ የነበረው የንግድ እንቅስቃሴ በዚያ ሳያበቃ በተለያዩ ማዕዘናት እያበቡ በመጡ ከተሞችም ይኸው ተቀጠጥሎ ቀጥሎ እንደነበር አንጋፋ በሆኑ የብሔሩ ተወላጆች አንደበት ዛሬ ድረስ ይነገራል፡፡ በዚህ ረገድ አብዛኞች የተሳተፉበት የሸገር ገበያ እንደነበር ይነገራል፡፡ እንዲያውም በኢትዮጵያ የንግድ እንቅስቃሴ አረቦችን በመተካት ቀዳሚ ሚና ከተጫወቱት ኢትዮጵያውያን ጉራጌዎች ዋነኞቹ እንደነበሩ ብዙ አብነቶች ይነገራሉ፡፡የጉራጌ ብሄር በባህሉ በደረሰበት ሁሉ የህዝቡን ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ኑሮ ከማጎልበት መልካም ስነ-ልቦናዊ አስተሳሰብና አመለካከት ከመፍጠር በተጨማሪ በስነ-ምግባር የታነፀ ትውልድ ከማፍራት አንፃር ትልቅ አስተዋፅኦ እንዳበረከተ መረጃዎች ይጠቀማሉ፡፡ ለምሳሌ አንድ የብሔረሰቡ ተወላጅ በገጠርም ሆነ በከተማ ኑሮውን ለመግፋት ቢያቅተውና የገንዘብ ችግር ቢገጥመው የአካባቢው ተወላጆች ወይም ወዳጆቹ ተገናኝተው በመምከር እቁብ በማሰባሰብ እንዲሰራ የሚደረግ ሲሆን ምናልባት የሰውዬው ትጋት በሚገባ እስኪረጋገጥ በተለያዩ የጉልበት ስራዎች ወይም አገልግሎት በመስጠት ስራ ላይ በማሰማራት እንዲቆይ ሲደረግ ራሱን የማሻሻልና ሰው የመሆን ፍላጎቱ ታይቶ እቁብ ተሰብስቦ ለንግድ ስራ የሚሆን ገንዘብ ይሰጠዋል እንጂ ፀያፍ በሆኑ የልመናና የስርቆት ተግባራት ላይ እንደማይሰማራ ኢትዮጵያን ወገኖቹ ይመሰክሩለታለ፡፡
ዛሬ አድማሱ በመስፋፋት ላይ ያለው እቁብ የብር/የቀርሺ ዳማዳ እና እድር መሰረታቸው በቀደሙት አመታት በእናቶች የተጀመረው ውጆ/የቅቤ ወይም የወተት ዳማዳ/ እንደሆነ በእሴቱ ባለቤቶች ይነገራል፡፡ በአነስተኛ የስራ መስክ ከተሰማሩት ጀምሮ በከፍተኛ የንግድ ስራ ላይ የሚገኙት የከተማ ነዋሪዎች በሳምንት ውስጥ ባሉት በተወሰኑ ቀናቶች እቁብ ያሰባስባሉ የተሰበሰበው የእቁብ ገንዘብ በየጊዜው እጣ ለወጣለት ሰው የሚሰጠው ሲሆን ገንዘብ የሚሻ ጉዳይ የገጠመው የእቁቡ አባልም የባለተረኛውን እጣ በመግዛት የንግድ ስራውን በማከናወን ይጠቀምበታል፡፡
ብዙ ግለሰቦች ከምንም ተነስተው በተሰበሰበላቸው የእቁብ ገንዘብ ስራ ፈጥረው ባለሀብት ሆነዋል፡፡ ከራሳቸው አልፈው ለሌሎች ወገኖቻቸው የስራ እድል ፈጥረዋል፡፡ ከኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታው ባሻገር እቁብ በከተማ ነዋሪዎች ዘንድ በመተሳሰብ ላይ የተመሰረተ ማህበራዊ ግንኙነታቸውን እንዳጠናከረላቸው የማህበራዊ እሴቱ ተጠቃሚዎች ይመሰክራሉ፡፡በተመሳሳይ የተለያየ ድንገተኛ ችግር፣ሀዘንም ሆነ ደስታ ሲገጥማቸው የሚጠያየቁበት የሚተሳሰቡበትና የሚረዳዱበት ማህበራዊ ተቋም እድር በመመስረት ቀዳሚ ስፍራ እንዳላቸው ይታወቃል፡፡ ዛሬ ዛሬ እነዚህ የብሔረሰቡ ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ትስስሮች ከራሱ አልፎ ወደ ሌሎች የኢትዮጵያ ብሔር ብሔረሰቦች መሸጋገራቸውና ኢትዮጵያዊ ገጽታ ተላብሰው መስፋፋታቸው በሀገር ልማት ላይ የተጫወቱት አዎንታዊ ሚና የትየለሌ ነው፡፡ደቦ/ጅጊ፣ጌዝ
በጉራጌ ባህል ጌዝ/ጅጊ/ አልፎ አልፎ ደግሞ ደቦ የሚባለው ወንዶች ወይም ሴቶች ጉልበታቸውን በማስተባበር በግለሰብ ደረጃ ብዙ ጊዜ የሚፈጁና ሊከናወኑ የማይችሉ ለምሳሌ የእርሻ ስራ፣የሰብል አሰባሰብ፣የቤት ስራ እና ለቤት ምንጣፍና ለመኝታ አገልግሎት የሚውሉ የቀርከሃ፣የእንሰት ውጤት፣የስንደዶ፣የቃጫና የዘንባባ ውጤቶች የሚያመርቱበት ማህበራዊ ህይወት ነው፡፡ ለምሳሌ እናቶች የእንሰት ውጤቶችን ሲሰበስቡ/እንሰት ሲፍቁ/ የሚተጋገዙበት ባህል ኡሳቻ ይሉታል፡፡ በአካባቢው የምትኖር የትኛዋም እናት ሆነች ሴት እንሰት ሲፋቅ በኡሳቻ/በደቦ/ ስራ በመገኘት የማህበራዊ ህይወት ተሳታፊነቷን በተግባር ታሳያለች፡፡ እንዲሁ ደግሞ የጅባ ስራዎች/የወለል ምንጣፍ/ ለምግብ ማቅረቢያና ለተለያዩ አገልግሎት የሚውሉ ቁሳቁሶች የሚሰሩት በጌዝ/ጅጊ/ በደቦ ነው፡፡
በተለይ በታህሳስና ጥር ወር እንሰትን በዋና ምግብነት የሚጠቀም የጉራጌ ገበሬ ከትንሹ እስከ ትልቁ የእንሰት አይነት ስፍራን የሚያዘጋጅና የሚተክል ሲሆን ይህም የሚከናወነው በጌዝ/ጅጊ/ ወይም በደቦ ነው፡፡ ከላይ በተጠቀሱት ወራቶች ትጉህ ገበሬ ብዙ ሰዎችን በደቦ በመጥራት ፏፏ ይቀብር/ለእንሰት ዘር የሚሆን ከአምቾ ጋር የተያያዘውን አካል አፈር ውስጥ ይቀብራል/ፏፏ ይፈዳ/ 1ኛ ደረጃ እንሰት ይበትናል፣ስሟ ይቀብር 2ኛ ደረጃ እንሰት ይተክላል/ጠቋት ይቀብር/ 3ኛ ደረጃ እንሰት ይተክላል/ሂባ ይቀብር/ ከፍተኛ ደረጃ እንሰት ወይም ወደ ዋናው የእንሰት ማሳ ወስዶ ይተክላል፡፡ ታዲያ በዚህ ሁሉ የሚሳተፈው ገበሬ የሚረዳዳበትና የሚተጋገዝበት ማህበራዊና ባህላዊ ስርዓት ጌዝ/ጅጊ/ ደቦ በመባል ይታወቃል፡፡
ወኪያ/ወቺያ/ የከብት ርቢ ስጦታ/ቆት/የፍየል፣የበግ፣የዶሮ ርቢ ስጦታ
የወኪያ/ወቺያ/ ባህል ብዙ ከብት ያሉት አንድ አርሶ አደር በጎረቤት በቅርብም ሆነ በሩቅ ለሚገኙ ከብት ለሌላቸው አርሶ አደር ወገኖቹ ከብት በመስጠት አርብተው ልጆቻቸውን በወተት እንዲያሳድጉና ከወተት በሚገኙ ተዋፅኦዎች ኑሮአቸውን እንዲደጉሙ ያስቻለ የመረዳዳትና የመደጋገፍ ባህል ነው፡፡ በወኪያ/ወቺያ/ የመተጋገዝ ባህል ከብት የተሰጠው አርሶ አደር በወተቱ ምርት ከመጠቀም ባለፈ የተራቡት ከብቶችን መውረስም ሆነ መሸጥ መለወጥ አይችልም፡፡ ከቅርብ ዓመታት ወዲህ የወኪያ ባህል አድጎ ወተት ከመጠጣትና ፍጉን ለእርሻቸው ከመጠቀም አልፎ የሚወለዱ ጥጃዎችን የጋራ ሃብት የማድረግ ጉዳይ እየተስፋፋ የመጣ ሲሆን ይህ ግን የሚሆነው ተደጋፊው ገበሬ ከብቶችን በማርባት ትጉህና ታታሪ መሆኑ የተመሰከረለት እንደሆነ ብቻ ነው፡፡
በዚህ በወኪያ ባህል የትኛውም ገበሬ ለአንድ ድሃ ገበሬ የሰጠው ከብት ሲያረጅ ተሸጦ ገንዘቡን ከመውሰድ ወይም ሌላ ተገዝቶ እንዲተካበት ከማድረግ ወይም ከብቱ ከሞተ የቆዳ ሽያጭ ዋጋ ከመቀበል በስተቀር ለሰጠው ከብት ምንም ዓይነት ጥቅም አይጠይቅም፡፡ በተለይ ከብት የተሰጠው አርሶ አደር በራሱ ፈቃድ ካልመለሰ ወይም የከብቱ ባለቤት ከአቅም በላይ የሆነ ችግር ካላጋጠመው በስተቀር ከብቱ እንዲመለስለት አይጠይቅም፡፡ ምናልባት ከአቅም በላይ በሆነ ችግር ከብቱን ቢሸጥ እንኳ የወኪያ ላም ተሰጥቶት ለነበረው ገበሬ ከሽያጩ ድርሻውን እንዲወስድ ያደርጋል፡፡ ይህ ካልሆነ ግን በባህሉ እስከ ዛሬ ይወገዛል፡፡ በቆላማው አካባቢ ደግሞ ላሞች በወቺያ እንደሚሰጡ ሁሉ ፍየል፣በግና ዶሮ ገዝቶ በመስጠት የሚወሰዱ ግልገሎችና ዶሮዎች በጋራ የመካፈል ስርዓት ቆት በሚል ይታወቃል፡፡
እነዚህ ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ፋይዳ ያላቸው አነስተኛና መለስተኛ የማህበረሰብ የመደጋገፊያና የመረዳጃ ባህላዊ እሴቶች ዘመናት አልፈው በሀገር ልማትና ኢኮኖሚያዊ እድገት ያበረከቱት አስተዋጽኦ ከፍተኛነት ሁሉም ኢትዮጵያዊ የሚቀበለው ሀቅ ሲሆን፣ይኸው አድማሱ ሰፍቶ በአጼዎቹ ዘመነ መንግስት በመንገድ አለመከፈት ምክንያት እንግልት ሲደርስበት የነበረው ጉራጌ ከወልቂጤ - ሆሳዕና እና ከአለምገና - ሆሳዕና እንዲሁም የምዕራብ ወረዳዎችን ሁሉ ከወልቂጤ ጋር በማስተሳሰር ግዙፍ ወደሆነ ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ፋይዳ ወዳለው የመንገድ ስራ ልማት ድርጅትነት መሸጋገሩ በአርአያነቱ የጎላ ሲሆን የብሔሩ አንፀባራቂ ታሪክ ሆኖ ኖሯል፡፡
እደ-ጥበብ
የሰው ልጅ የተፈጥሮ አካባቢውን ለራሱ ምቹ ለማድረግና ተፈጥሮ የቸረችውን ፀጋ ለመጠቀም ለዘመናት ባደረገው ተደጋጋሚ ጥረት የእደ-ጥበብ እውቀቱንና ክህሎቱን ማሳደጉ ይታወቃል፡፡ ይህን እውቀትና ክህሎት ደግሞ ከመነሻው ላይ ያገኘው በመደበኛ ትምህርት ሳይሆን ህይወቱን መልክ ለማስያዝ በየዕለቱ ካደረገው ትግበራውና ቀጥሎም ከትውልድ ወደ ትውልድ በተከናወነው ቅብብሎሽ መሆኑን በዘርፉ ጥናት ያደረጉ ተመራማሪዎች ይገልፃሉ፡፡ ሰው ከአካባቢና ከዚያ ውጪ የሚያገኛቸውን ልዩ ልዩ ግብዓቶችንና የማምረቻ መሳሪያዎችን በመጠቀም ለቁሳዊና መንፈሳዊ ፍላጎቶቹ መሟላት የሚጠቀምባቸውን ቁሳቁሶችና መሳሪያዎች ያዘጋጅ እንደነበር ይታወቃል፡፡
የጉራጌ ብሔር የሰው ልጅ ተፈጥሮን ለርሱ በሚመቸው ዓይነት መልኩ መግራት ከጀመረበት ዘመን አንስቶ የተፈጥሮ አካባቢው የሚገኙ ግብዓቶችን በመጠቀም ለየዕለት ህይወቱ አስፈላጊ የሆኑትን ቁሶች ከማምረት በመለስ ለረጅም ጊዜ አገልግሎት ሊሰጡ የሚችሉ የምርት መገልገያዎችን ጭምር በመስራት እውቀቱን ለትውልድ አሸጋግሯል፡፡ ከእነዚህ የብሔሩ መለያ ናቸው የሚባሉት የእደ-ጥበብ ውጤቶች መሃል ጥቂቶቹን ለአብነት እንኳብንጠቅስእንደ የብረት፣የሸክላ፣የእንጨት፣የቀንድ፣የሽመና፣የቆዳ፣የቃጫ፣የስንደዶ፣የቄጠማ …ወዘተ ስራዎች እናገኛለን፡፡ የብሄሩ እውቀትና ክህሎት አሻራ በእነዚህ የእደ-ጥበብ ዘርፎች አርፎባቸዋል፡፡ ዛሬ ዛሬ በጉራጌ ዞን በሚገኙት አንዳንድ ወረዳዎች ከስንደዶ፣አክርማ፣ቃጫና ክር የሚመረቱ የእደ-ጥበብ ውጤቶች ከአካባቢውና ከአገር አልፈው ከባህር ማዶም ባሉት ገበያዎች ላይ ተፈላጊነታቸው በየጊዜው እየጨመረ መጥቷል፡፡ እኛም በዚህ ጽሑፍ ውስጥ የጉራጌ ብሔር እደ-ጥበብ ናቸው ከሚባሉት መሃከል ዋና ዋናዎቹን መርጠን ለማሳየት እንሞክራለን፡፡
ይወደረ

በኧሰት አብቃይነቱ የሚታወቀው የጉራጌ ብሔር እንሰትን ከምግብነት በተጨማሪ ለተለያዩ ግልጋሎቶች ሲጠቀምበትይስተዋላል፡፡ጉራጌ ለምግብ ማዘጋጃነትና ማቅረቢያነት፣ለመኝታና ለቤት ውስጥ ንጣፍነት …ወዘተ የእንሰት ውጤትን ይጠቀማል፡፡
ይወደረ ለምግብ ማቅረቢያነት የሚያገለግል ሲሆን የሚሰራውም ከእንሰት በተገኘና የተለያየ ቀለማትን በተነከረ ቃጫ እና ክር ነው፡፡ አንድ ጥሩ የተባለ ይወደረ ሰርቶ ለማውጣት እስከ አንድ ወር ያህል ጊዜ የሚፈጅ ሲሆን እንዲህ አይነቱ ይወደረ ቁመቱ 2 ሜትር ጎኑ/ስፋቱ/ ደግሞ 1 ሜትር ያህል ይሆናል፡፡ይወደረ በተለይ ትላልቅ ክብረ-በዓላትና ሰፊ የሆነ ዝግጅት ሲኖር ቤት ውስጥ ወለል ላይ በተነጠፈ ሰፊና ምርጥ ጅፐ/ጅባ/ ላይ ይዘረጋና ቆጮ፣ክትፎ፣አይብ፣የጎመን ክትፎ …ወዘተ በጣባ ወይም በጥለስ(ከኧሰት ቅጠል የተሰራ ለመመገቢያነት የሚያገለግል) እንዲበላበት ለታዳሚው ይዘረጋል፡፡ በተለይ በመስቀል ወይም በአረፋ ክብረ-በዓላት ጊዜ ይወደረ እንዳይቆሽሽ ተጠቅልሎ በንጽህና ከተቀመጠበት ቦታ ይወጣና እስከ በዓላቱ ፍፃሜ ድረስ ጅፐ ላይ ተዘርግቶ ማዕድ ማቅረቢያ ሆኖ ሲያገለግል ይቆያል፡፡
ጅፐ(ጅባ)
ሌላው ከኧሰት ተክል እና ከቄጤማ የሚሰራው የእደ-ጥበብ ውጤት ጅፐ/ጅባ/ ይባላል፡፡ ይህ የእደ-ጥበብ ውጤት ከኧሰት ተክል ከሚገኘው ቃጫና ኮባ የሚሰራ ሲሆን ለቤት ውስጥ ወለል ንጣፍነትና ለመኝታ አገልግሎት ይሰራል፡፡ የተለያየ መጠንና ጥራት ያላቸው የጅፐ አይነቶች ሲኖሩ በጣም ምርጥ የተባሉት ልክ እንደ ይወደረ ለተለያዩ ክብረ በዓላትና ለትላልቅ ዝግጅቶች ብቻ ግልጋሎት የሚሰጡ ናቸው፡፡ መሃከለኛ የሆኑት ደግሞ ዘወትር ተነጥፈው በህዝቡ የእለት ተዕለት ህይወት ውስጥ ጥቅም ላይ ይውላሉ፡፡
ሰፍ/መሶብ/

ሰፍ/መሶብ/ ከሰንደዶ እና ከአክርማ የሚሰራ ሲሆን በጉራጌ ብ/ሰብ ዘንድ የተለያየ ቅርፅና መጠን ያላቸው ሰፍ/መሶብ/ሌማት/ እየተሰሩ ለተለያዩ የማዕድ አገልግሎቶች ሲውሉ ይስተዋላሉ፡፡ እነዚህ በልዩ ልዩ ህብረ ቀለማት ያጌጡ ውብና ማራኪ የእደ-ጥበብ ውጤቶች ከቡና ቁርስ ማቅረቢያነት እስከ እንጀራ፣ዳቦ … ወዘተ ማስቀመጫነት፡፡ ሲያገለግሉ ትላልቅ ሆቴሎችና ሬስቶራንቶችም በዋናነት ይጠቀሙባቸዋል፡፡
ልዩ ልዩ የሸክላ ምርቶች

በጉራጌ ብሔረሰብ ውስጥ እጅግ መጠነ ሰፊ ግልጋሎት የሚሰጡ የሸክላ ስራ ውጤቶች ይገኛሉ፡፡እነዚህየእደ-ጥበብ ውጤቶች ለምግብ ማብሰያነትና ማቅረቢያነት፣ለመጠጪያነትና ማቅረቢያነት፣የሚበሉና የሚጠጡ ምግቦችንና መጠጦችን ሳይበላሹ ለረጅም ጊዜ ማቆያነት/ማስቀመጫነት/ …ወዘተ የሚጠቅሙ ሲሆን አንዳንዶቹም ከአንድ በላይ ለሆነ ጠቀሜታ ይውላሉ፡፡ እንደ ጀበና፣የክትፎና አይብ …ወዘተ ማቅረቢያና ማዋሃጃ ጣባ፣ቅቤ ወይም ማር ወይም ወተት ማስቀመጫ፣ጥዋ፣የሸክላ ድስጥ፣እንስራ፣ጋን … ወዘተ ታዋቂ የብሔሩ የእደ-ጥበብ ውጤቶች ናቸው፡፡
አንቀፎ/ማንኪያ/

ጉራጌ ከከብት ቀንድ የተለያዩ የቤት ቁሶችን ይሰራል፡፡ ከነዚህም ውስጥ አንዱና ዋነኛው አንቀፎ/ማንኪያ/ ነው፡፡ አንቀፎ የተለያየ መጠን ያለው ሲሆን አነስተኛው ለክትፎ፣አይብ፣ ዝማሙጃት ኧቋት፣ፍንታንፍንቶ፣ኦዛት፣ድኩቸ፣የማር ወለላ… ወዘተ መመገቢያነት ሲያገለግል ትልቁ ደግሞ በትልቅ ጣባት ክትፎ፣አይብ፣ዝማሙጃት፣የጎመን ክትፎ … ወዘተ የመሳሰሉትን ከቅቤና ሚጥሚጣ ጋር ለመለወስ ለማቀላቀል ይጠቀሙበታል፡፡