ጉራጌ ዞን
የጉራጌ ዞን ታሪካዊ ቦታዎች
ምሁር ኢየሱስ ገዳም

ሀገራችን ኢትዮጵያ የተለያዩ ሀይማኖቶች ፣ ብሔር ብሔረሰቦችና ህዝቦች ተቻችለው የሚኖሩባት ሀገር ናት፡፡ በጉራጌ ዞንም ይኸው እውነታ ይስተዋላል፡፡ ሀይማኖታዊ ተቋማቱም ከቤተ እምነትነት ባለፈ መልኩ የእምነቱ ተከታዮችንና ቱሪስቶችን የማማለል አቅም ያላቸው የተለያዩ ታሪኮች፣ ታሪካዊ ቅርሶችና ባህላዊ እሴቶችን የያዙ ናቸው፡፡ ቱሪስቱም ለመጎብኘት፣ምሁራኑም ለጥናትና ምርምር ወደ እነዚሁ ስፍራዎች ይንቀሳቀሳሉ፡፡
ምሁር ኢየሱስ ገዳም የሚገኝው በምሁር አክሊል ወረዳ ቆረር ቀበሌ ውስጥ ሲሆን ከአዲስ አበባ በ207 ኪ.ሜ፣ ከዞኑ ዋና ከተማ ወልቂጤ በ52.ኪ.ሜ፣ ከወረዳው ዋና ከተማ ሀዋርያት 3ኪ.ሜ ገባ ብሎ በስተሰሜን ምስራቅ በኩል ይገኛል፡፡ሀገራችን ኢትዮጲያ ካሏት በርካታ ጥንታዊና ታሪካዊ ገዳማት መካከል በዋናነት ተጠቃሽ ሲሆን ቤተ ክርስቲያኑ ከዘመነ ዮዲት ጉዲት በፊት በ804ዓ.ም የተተከለ ነው፡፡ በገዳምነት የተመሰረተው/ የተገደመው / በኢትዮጵያዊው ፃዲቅ አባት በአቡነ ዜና ማርቆስ በ13ኛ መ.ክ.ዘ /በ1250ዓ.ም/ መሆኑን መዛግብት ይጠቁማሉ፡፡ ገዳሙ በትክክል በ91º17’47 ሰሜን ኬክሮስ መስመርና በ39º99’20 ምስራቅ ኬንትሮስ መስመር ላይ አርፏል፡፡ አካባቢው ከባህር ጠለል በላይ ያለው ከፍታ 2330 ሜትር ነው፡፡ የገዳሙ የይዞታ ስፋት ወደ 10 ሄክታር የሚጠጋ ሲሆን በጠቅላላው 3 ትላልቅ ግቢዎች ሲኖሩት እነዚህም ግቢዎች እንደገና በተለያዩ ትናንሽ ግቢዎች የተከፋፈሉ ናቸው፡፡ እነዚህም የዘመናዊ ትምህርት ቤት ግቢ፣ የመንፈሳዊ ትምህርት ቤት ግቢ፣ የካህናት ማሰልጠኛ ግቢ፣ ሙዝየም ግቢ፣ የሴቶች መነኩሳት ግቢ፣ ዋናው የቤተክርስቲያኑ ግቢ፣ የወንዶች መነኩሳት ግቢ፣ የፈረንጅ ላሞችና የአበሻ ላምች ግቢ ናቸው፡፡የገዳሙን ረጅም ዕድሜ የሚያወሱ ብዛት ያላቸው ህያው ሀገር በቀል የዝግባ፣የወይራ፣የፅድ ወዘተ ተፈጥሮአዊ ቅርሶች እጅብ ብለውና ግርማ ሞገስ ተላብሰው ወደ ገዳሙ የሚመጣውን ሰው በመጀመሪያ እንኳን ደህና መጣችሁ ብለው ይቀበሉታል፡፡ሌላው በገዳሙ ውስጥ ጥንታዊነቱን፣ ታሪካዊነቱን የሚያመላክቱ ተዳሳሽና የማይዳሰሱ ቅርሶች ይገኛሉ፡፡ እነዚህም በገዳሙ ሙዚየም ውስጥ ከሚገኙት ቅርሶች መካከል ለመጥቀስ ያህል የብር መስቀል፣ የብራና መፃህፍት፣ መቁራሪት፣ ጽዋ፣ ደወል፣ የጥንት የቤተክርስቲያን ሊቃውንት ካባ፣ መለከት/ጡርንባ/፣ ውዥግራና ራስማር ጠመንጃዎች፣ ከአንድ ወጥ እንጨት ተፈልፍሎ የተሰራ የመጾር መስቀል፤የዳዊትን ታሪክ የያዘ በስእላዊ መልክ የተዘጋጀ መፅሐፍ ከነማህደሩ፤የነገስታት ደብዳቤዎች … ወዘተ ይገኛሉ፡፡ እንዲሁም ከተለያዩ ሀገሮች በገጸ በረከትነት የተሰጡ በርካታ ንዋየ ቅድሳትና ቅርሶች የሚገኙ ሲሆን ለአብነት በ1990ዓ.ም ከሊባኖስ ለገዳሙ የተበረከተ የእጅ መቁጠሪያ ፣ከግሪክ ኦርቶዶክስ ቤ/ክርስቲያን ሊቀ ጳጳስ አቡነ ሱራፊ የተበረከተ የግሪክ ስዕል፣ የተለያዩ ጌጣጌጦችን፣ የሰጎን እንቁላል እና መብራት ያላቸው መስቀሎች፣ ከግብፅ ኦርቶዶክስ ቤ/ክርስቲያን ሊቃነ ጳጳስ አቡነ ኢንቶኒዮስ የተበረከቱ የቤተ መቅደስ መገልገያ ጽዋ የስነ-ስቅለት ምስል ያለበት መስቀል ይገኛሉ፡፡ እንዲሁም በ18ኛው መቶ ክፍለ ዘመን የኢትዮጲያ ሰዓሊያን በእንጨት ላይ የሳሏቸው ስዕሎች፣ ኢትዮጲያ ፓትሪያርክ መሾም ከጀመረበት ጊዜ አንስቶ የነበሩና አሁን ያሉ ፓትሪያርኮች ፎቶግራፍ በሙዝየሙ ውስጥ ይገኛሉ፡፡
የአብሬት መስጅድ

የአብሬት መስጅድ በጉራጌ ዞን ቸሃ ወረዳ ውስጥ የሚገኝ ሲሆን ከአዲስ አበባ 210 ኪ.ሜ ከዞኑ ርዕሰ ከተማ ወልቂጤ 52 ኪ.ሜ ርቀት ፣ከወረዳው ርዕሰ ከተማ እምድብር 20 ኪ.ሜ ርቀት ላይ ይገኛል፡፡አብሬት መስጅድ ከዛሬ 135 ዓመት በፊት በዳግማዊ አፄ ሚኒሊክ ዘመነ መንግስት በታላቁ ሼህ ቡሽራ ኢብራሂም እንደተመሰረተ ታሪክ ይዘክራል፡፡ እኚህ ታላቁ የሃይማኖት አባት የእስልምና ሃይማኖት ለማስፋፋት በነበራቸው ጽኑ ፍላጎት ወሎ ክፍለ ሃገር ውስጥ ወደሚገኘው ዳና በመሄድ በዳና ሼህ አማካኝነት የእስልምና ትምህርት(የቁርዓን፣የሀዲስ እና የፊቂህ) ተምረው ከተመረቁ በኋላ ወደ ትውልድ አካባቢያቸው በመመለስ ከአካባቢው ህብረተሰብ ጋር በመተባበር መስጂዱን መመስረት ችለዋል፡፡ ይህ መስጅድ በቤተ ጉራጌ ውስጥ ከሚገኙ ቀደምት መስጅዶች መካከል አንዱ እንደሆነ ይነገርለታል፡፡በሼህ ቡሽራ ኢብራሂም የተመሰረተው የአብሬት መስጅድ ልጃቸው ሼህ ሰይድ ቡድላ ተቀብለው ይበልጥ በማጠናከርና በማልማት እሳቸው ደግሞ ለልጆቻቸው በማስተላፍ በአሁኑ ወቅት እጅግ በተሻሻለ መልኩ አገልግሎት እየሰጠ ይገኛል፡፡ መስጅዱ ዘላቂ እና የነባር የእስልምና ትምህርት ማዕከልና የቱሪስት መዳረሻ ለማድረግ እየሰራ ይገኛል።በዚህ መስጅድ ውስጥ የተለያዩ ቅርሶች ማለትም ጥንታዊ ጋሻዎች ፣ጎራዴዎች ፣ጦር፣በብራና የተፃፉ ቁርአኖችና ክታቦች፣የተለያዩ የትርጉም ስራዎች፣ የእንጨት መጻፍያ (ሉህ) እና በብራና የተጻፉ የነገስታቶች ታሪክ የሚያወሳ (ፊትሁል ሀበሻ) መፅሃፍ ይገኛሉ፡፡የአብሬት መስጅድ ቅጥር ግቢ ለጎብኚዎች ምቹና ማራኪ ከመሆኑም ባሻገር ቁጥራቸው እስከ 800 የሚደርስ ኃይማኖታዊ ትምህርት መማርያና የእንግዳ ማረፍያ በሆኑ አነስተኛ መስጅዶችና ኸላዋዎች የተሞላ ነው፡፡መስጅዱ የእስልምና ኃይማኖት ከማስፋፋትና ከማጠናከር አንፃር የቁርዓን ንባብና ትርጉም (ተፍሲር)፤ ተጅዊድ፤ ተውሂድ፤ ፊቅህና ሀዲስ ትምህርት በመስጠት እምነቱ ይዘቱን ሳይለቅ ለተከታይ ትውልድ በማስተላለፍ በኩል የጎላ ሚና አለው፡፡በመስጅዱ በመቶዎች የሚቆጠሩ ተማሪዎች በአዳሪና በተመላላሽ መልኩ ይማሩበታል፡፡
የአብሬትመውሊድ በዓል በዓመት ሁለት ጊዜ የሚከበር ሲሆን በተለይ የብሔራዊ መውሊድ በዓል ተከትሎ የሚከበረው ዓመታዊ በዓል በርካታ (ከ20 ሺህ በላይ) ከሀገር ውስጥና ከሀገር ውጪ በሚመጡ የእምነቱ ተከታዮችና ጎብኚዎችይታደማሉ፡፡የአብሬት መስጅድ ለመጎብኘት ሲመጡ እግረ የጉራጌ የጥበብ ውጤት የሆነውን ጀፎረን እንዲሁም መልክዓ ምድር አቀማመጥ እያደነቁ የአፍጥር ጥቅጥቅ የተፈጥሮ ደን በቅርብ ርቀት አሻግረው እየተመለከቱ ይዝናናሉ፡፡
ኤነር አማኑዔል ገዳም

ገዳሙ የሚገኘው በእነሞርና ኤነር ወረዳ ኤነር ቀበሌ ውስጥ ነው፡፡ ከወልቂጤ 70 ኪ.ሜ፣ከጉንችሬ 35 ኪ.ሜ ርቀት ላይ ወደ ቆሴ በሚወስደው መንገድ በስተምዕራብ በኩል 400 ሜትር ገባ ብሎ ይገኛል፡፡የገዳሙ ቅጥር ግቢ እንደገቡ ከመቶ ሃያ ዓመት በላይ እድሜ ያስቆጠረውን የአማኑኤል ታቦተ ህግ ማረፍያ ደብርና ሌሎች ሁለት የዘመናዊ ህንፃ ውጤቶች የሆኑ ቤተክርስቲያናትን አምረውና ተሰንግለው ይመለከታሉ፡፡ የኤነር አማኑኤል ታቦተ ህግ በስምንተኛው መቶ ክፍለ ዘመን ገደማ ወደ ምድረ ጉራጌ እንደመጣ መረጃ የሰጡን የደብሩ የበላይ ጠባቂዎች ይገልጻሉ፡፡ የአማኑኤል ታቦትን አመጡ ከሚባሉት መካከል አዝማች ወያዞ፣አዝማች እነጋሪ፣ቄስ ኪዳኔ ፣ጎንግ የተባሉት ተጠቃሽ ናቸው፡፡ በአካባቢው የኤነር አማኑኤልን ታቦተ ህግ ተከትሎ ክርስትና እንዲስፋፋ አድርገዋል፡፡በገዳሙ በርካታ ዘመናትን ያሥቆጠሩ የወቅቱን የስልጣኔ አሻራ የሚያሳብቁ ድጓዎች፣ ግንዘቶች፣ ¾Sï` SekKA‹፣ታምረ ኢየሱስ፣ መፃፈ ሰዓታት ፣ አርባአቱ ወንጌላዊያን ፣ ፀሎተ ፍታት ፣ መጽሐፈ ቅዳሴ ፣ ድርሳነ ገብርኤል፣ ድርሳነ ሚካኤል (ስእላት ያሉት) .... ወዘተ፣ የመሳሰሉት ቅዱሳት መጽሐፍት በብራና ተጽፈው ይገኛሉ ፡፡ በተጨማሪም ከንግስት ዘውዲቱ የተሰጠ ቀሚስ፣በወቅቱ ከጎንደር እንደመጡ የሚነገርላቸው መስቀሎች፣ለየት ያለ ፅላት፣ የታላላቅ መሳፍንታትካባዎች ፣ላንቃ፣የአቡነ ባሲሊዮስ የብር መስቀል፣ ጥንታዊ ከበሮ፣ፅዋዎች፣ፅናፅሎች ባጠቃላይ የነገስታት አልባሳት እንዲሁም ለፀሎት የሚያገለግል ፍልፍል ዋርካም በገዳሙ ቅፅር ግቢ ውስጥ ቅርንጫፎቹን አንዠርግጎ ይገኛል፡፡የኤነር ቀበሌ ገበሬ ማህበር ከገዳሙ ጋር ተያይዞ ሁለት ጥንታዊ ዋሻዎች ይገኙበታል ፡፡ አንደኛው ከገዳሙ በቅርብ ርቀት ላይ የምናገኘው የአዝጋታር ዋሻ ነው፡፡ ዋሻው በ15ኛው መቶ ክፍለ ዘመን በአህመድ ግራኝ ሃይማኖታዊ ቅዋሜ የተነሳ በወቅቱ የነበሩት ክርስቲያኖች (የኦርቶዶክስ እምነት) ተከታዮች ዋሻውን አበጅተው ቅርሳቱን ለመታደግ እንደተቻለ መረጃዎች ያመለክታሉ፡፡ ዋሻው አሁንም ድረስ በታሪክነቱ ህያው አሻራውን ይዟል፡፡ ከ460 ዓመት በኋላ የደበቀውን የኤነር ጎሳ ቅርስ ታቦተ አማኑኤልን በዳግማዊ አፄ ሚኒሊክ እና በአከባቢው ተወላጅና የጎሳ መሪ ጋዳጋሎ አማካኝነት ከዋሻው እንዲወጣ ተደርጓል፡፡ ይህ ከሆነ በኋላም ለታቦተ ህጉ ማረፊያ ‹‹ አዝጋተር›› (የአሁኑ ስፍራ) ገዳም እንዲገደምለት መደረጉን የደብሩ እድሜ ጠገብ አዛውንቶች ይገልፃሉ፡፡ ሌላኛው በአስራ ሁለተኛው መቶ ክፍለ ዘመን እንደተሰራ የሚነገረው ‹‹ የመላዕኬ›› ዋሻ ነው፡፡ ዋሻዎቹ ጥልቅ ምርምር የሚሹ ናቸው፡፡
ቆጠር ገድራ ቅድስት ኪዳነምህረት ገዳም

ቆጠር ገድራ ቅድስት ኪዳነምህረት ገዳም በእዣ ወረዳ የሚገኝ ሲሆን ከዞን ርዕሰ ከተማ ወልቂጤ 52 ኪ.ሜ ከወረዳዉ ርዕሰ ከተማ አገና በምስራቅ አቅጣጫ 10 ኪ.ሜ ርቀት ላይ 320 ሄ/ር በሚሸፍን የቆጠር ገድራ ሀገር በቀል ጥብቅ የተፈጥሮ ደን ውስጥ ይገኛል፡፡ ቆጠር ገድራ ስያሜው ያገኘው ከጉራጊኛ ቃል ሲሆን ይኸውም ቆጠር የሚለው በአካባቢው የሚኖር የጎሳ ስም ሲያመላክት ገድራ ደግሞ አስታ የሚባል ቁጥቋጦ አይነት መጠሪያ ነው፡፡
ቆጠር ገድራ ተዳፋታማ በሆነ ስፍራ የሚገኝ ሲሆን ብዛት ባላቸው ሀገር በቀል ዛፎች ማለትም ዝግባዎች፣የኮሶ ዛፍ፣የሀበሻ ፅድ …ወዘተ የሚገኙ ሲሆን የቆጠር ገድራ የተፈጥሮ ደን ለረጅ ዘመናት ከሰው ንኪኪ ተጠብቆ የቆየው በአካባቢው ኅብረተሰብ ነባር ባህል መሠረት የጥንት አባቶች ደኑ እንዳይቆረጥ በቃል ኪዳን/ጉርዳ/ ስለተሳሰሩ ነው፡፡ በቆጠር ገድራ ደን ውስጥ በ2003 ዓ.ም ቆጠር ገድራ ቅድስት ኪዳነምህረት ቤተክርስቲያን ለመስራት መሠረት ድንጋይ ተቀምጦ በዚያኑ ዓመት ቤተክርስቲያኑም ተሰርቷል ፡፡ ይህ በእንዲህ እንዳለ በ2004 ዓ.ም አባ ገብረ ክርስቶስ የሚባሉ ባህታዊ ከአማራ ክልል ጣና ሀይቅ ከሚገኙ ደሴቶች አንዱ ከሆነው ከጣና ቂርቆስ ገዳም መጥተው በቆጠር ገድራ የተፈጥሮ ደን ውስጥ ዋሻዎች እንዳሉ በራዕይ እንደታያቸው በወቅቱ ለጉራጌ ሀገር ስብከት ስራ አስኪያጅ እንዳስታወቁ መረጃዎች ይጠቁማሉ፡፡ በዚህም በሀገር ስብከቱና በሚመለከታቸው አካላት ባህታዊ አባ ገብረ ክርስቶስ ከአካባቢው ህብረተሰብ ጋር በመሆን ዋሻዎቹን እንዲከፍቱና ቅርሶች እንዲያወጡ ተፈቀደላቸው፡፡ በዚሁ መሠረት በቆጠር ገድራ የተፈጥሮ ደን ውስጥ በተለያዩ ስፍራዎች በቁጥር አስር ዋሻ ቤተመቅደሶች ተገኝተዋል፡፡ ለዘመናትም ሳይታወቁ ሚስጥርና ስውር ሆነው እስከ 2004 ዓ.ም ቆይተዋል፡፡በደኑ ውስጥ ከተገኙት ዋሻዎች ከአንዱ ዋሻ ወደ ሌላኛው ዋሻ ለመሄድ በመካከላቸው ያለው ርቀት በአማካይ አንድ ኪሎ ሜትር ይሆናል፡፡በቆጠር ገድራ ኪዳነምህረት ገዳም ዋሻዎች ውስጥ እርጅና የተጫጫናቸው እና በአደራ የተቀመጡ የሚመስሉ ብዛት ያላቸው የተለያዩ ኃይማኖታዊና ታሪካዊ ቅርሶች ተገኝተዋል፡፡ እነዚህም የጥንት ፅሁፎች እና የመስቀል ቅርጽ ያላቸው ስዕሎች፣ ሀይማኖታዊ ስርዓት / የኦርቶዶክስ/ መፈፀሚያ ከሆኑት መገልገያዎች የነሀስ ፅዋ፣ የነሀስና የእንጨት መስቀሎች፣ የእንጨት መቋሚያ/ መደገፊያዎች/ ፣የብራና ላይ ስዕሎች፣ የቀለም መንከሪያ ብዕር፣ በእብነ በረድ ድንጋይ ላይ ተቦርቡሮ የተሰራ የሶስት ቅዱሳን አባቶች ምስል፣ የነገስታት ማህተሞች፣ የኦሪት መሰዊያ ናቸው ተብሎ የሚገመቱ ምጣዶች ወዘተ… ቅርሶች ተገኝተዋል፡፡ እነዚህ የተገኙ ቅርሶች ለደህንነታቸው አመቺ በሆነ ስፍራ እንዲቀመጡ ተደርጓል፡፡ ከተገኙት አስር ዋሻዎች ሰባቱ ለጉብኝት ክፍት የተደረጉ ሲሆን እነሱም ደብረ ቢዘን፣ ቤተ ጎልጎታ፣ ቤተ መድህን ፣ ቤተ ጠበብት፣ ቤተ ኤፍራታ፣ ቤተ ደብረ ብርሃን ፣ቤተ ደናግል በማለት ስያሜ የተሰጣቸው ናቸው፡፡ ባጠቃላይ በስፍራው የተገኙት ዋሻዎች ተመሰረቱ ተብሎ የሚገመተው በ6ኛው መቶ ክፍለ ዘመን በነበሩት ቅዱሳን አባቶች መካከል አንዱ በሆኑት በአባ ማቲያስ እንደሆነና በስፍራው ገዳማዊ አገልግሎት እንዳስጀመሩ ይወሳል፡፡ እነዚህ አስሩ የዋሻ ቤተ መቅደሶች እና ቅርሶች በተገኙበት ቆጠር ገድራ የተፈጥሮ ደን ውስጥ በአሁኑ ወቅት በገዳምነት ተገድሞ/ተመስርቶ/ ኦርቶዶክሳዊ የሀይማኖት ስርዓት እየተከናወነበት ከመሆኑም ባሻገር አዳሪ የኃይማኖት ት/ቤት /አብነት ት/ቤት/ ተከፍቶ ተማሪዎችን ተቀብሎ በኃይማኖታዊ ትምህርት እየሰጠ ይገኛል፡፡ ስፍራውም በአቡነ ቀሌሜንጦስ የጉራጌ፤ ከንባታ፤ ሀድያና ስልጤ ሀገር ስብከት ሊቀ ጳጳስ በ2004 ዓ.ም በገዳምነት ተገድሟል፡፡ ዘመናዊ ህንፃ ቤተክርስቲያንና ኃይማኖታዊ ትምህርት ቤትም ለመገንባት ታቅዷል፡፡ በገዳሙ በዓመት ሦስት ጊዜ የሚከበሩ ክብረ- በዓላት አሉ፡፡ እነሱም የካቲት 16፤ሰኔ 30 (የመጥመቁ ዮሃንስ በዓል) እና ነሐሴ16 የሚከበሩት ክብረ-በዓላት ሲሆኑ በእነዚህ በዓላት ወቅት ከተለያዩ የሀገሪቱ ክፍሎችና አቅጣጫዎች የፆም ወራትን እና የእረፍት ቀናትን አስታከው በሚመጡ የእምነቱ ተከታዮች የሚጎበኝ ሲሆን በተለይ በየዓመቱ የካቲት 16 ደማቅ በዓል ላይ ቁጥራቸው እስከ 25000 የሚደርሱ ጎብኚዎች ይታደማሉ፡፡++
ቆጠር ገድራ ኪዳነምህረት ገዳምን ሲጎበኙ አካባቢውን ከሸፈነው ጥብቅ የተፈጥሮ ደንን ጨምሮ በኢትዮጵያዊው ቅዱስ አባት አቡነ ተክለሃማኖት እንደተተክለ የሚነገርለት ጥንታዊ የእንጨት መስቀል፣የዋሻዎቹ ውበትና በዋሻዎቹ መካከል ያለው የውስጥ ጉዞ፣በአካባቢው የሚገኘውና ታዋቂው የመድኃኒዓለም ቤተክርስቲያን፣ከዞኑ ርዕሰ ከተማ ወልቂጤ ጀምሮ የወልቂጤ ዩንቨርሲቲ፣ቲናው አበባ አክሲዮን ማኅበር፣ገጨ ቅዱስ ሩፋኤል ገዳም፣አገና ከተማና በዙሪያው ያለው ተፈጥሮ ደን እና ትረር ፏፏቴን እየጎበኙ ይዝናናሉ፡፡