የምስራቅ ጉራጌ ዞን ባህላዊ መስህብ
የምስራቅ ጉራጌ ዞን ባህላዊ መስህብ
ጎርደና
ጎርደና ማለት በሶዶ ክስታኔ ቤተ-ጉራጌ ህዝብ ዘንድ ቤታቸውን ለመስራት በቀላሉ ከማይበሰብሱ ዕድሜ ጠገብ ከሆኑ የጽድ/የዛፍ ፍልጥ ይጠቀማሉ ይህንንም ጎርደና ተብሎ የሚጠራ ሲሆን ጎርደና ጠንካራ ፍልጥ ስለሆነ የመሸከም አቅሙ ከፍተኛ በመሆኑ ጉድጓድ ተቆፍሮ ጎርደናው በማቆም በጥሩ ማገር ተማግሮ ጣሪያው የሚያርፍበት ቦታ በትክክል እኩል ተቆርጦ ጣርያው ላይ ያሉ ጠርብ ማገር የጣርያው ክዳን ሌሎችም ይሸከማል፡፡ ጎርደና የሶዶ ክስታኔ ቤተ-ጉራጌ ማህበረሰብ ያቋቋሙትና ያደራጁት ጥንታዊ የአስተዳደር ሥርዓት ሲሆን ህዝቡ አንድነቱና ማንነቱን ጠብቆ እንዲኖርና በመሀላ የሚታሰር ባህላዊ ቃል-ኪዳን ነው፡፡

ሴራ
ማለት የሶዶ ክስታኔ ቤተ-ጎራጌ አባቶች አጭበር ተብሎ በሚታወቀው እና ልዩ ስሙ እንጆሪ በተባለው ስፍራ ላይ በመሰባሰብ የጎርደና ሴራ (ለሁሉም እኩል የሆነ ህግ) የተባለ ባህላዊ መተዳደርያ ህገ ደንብ አጸደቁ፡፡ በተጨማሪም የጎረቤታችውም የወለኔ የሀገር ሽማግሌዎችም በዚህ ተስማምተው እስከ አሁን ድረስ በጎርደና ሴራ እየተዳደሩ ይገኛል፡፡
የጎርደና ሸንጎ
ማለት የጎርደና ባህላዊ ህገ ደንብ (ሴራ) የሚጽድቅባቸው መማክርት ሲሆን የሁሉም የሶዶ ክስታኔ ቤተ-ጉራጌ ሸንጎ መማክርት በማህበረሰቡ የተወከሉ ታላላቅ የሃገር ሽማግሌዎችና የሴራ አባቶች እየተመከረባቸው የሚጸድቁ ህግጋቶችና ደንቦች (ሴራዎች) እዲፈጸሙ በተዋረድ በስሩ ለተዋቀሩት እዲያስፈጽሙ ለሀገር ሸንጎዎች የሚያስተላልፉ ሲሆን የየሀገሩ ሸንጎዎችም ተቀብለው በየበኩላቸው ላለው ህዝብ በተግባር እዲውል በማድረግ ከሀገር ሸንጎዎች በተዋርድ የሚገኙት በጣም ብዙ ሳቡኘቶች ወይም እድሮች የእዝ መስመራቸውን ጠብቀው በጎርደና ህገ ደንብ (ሴራ) መሰረት በተዋረድ ከጎርደና ሸንጎዎች የተላለፈላቸውን መተዳደሪያ ህጎችና ደንቦች (ሴራ) ህዝቡ በየ ሳቡኘቶቹ (እድሮች) እየደረሰው በሙሉ ፍቃደኝነት እየተቀበሉ ሲጠቀሙባቸው የኖሩ ሲሆን ዛሬም ቢሆን የጎርደና ህገ ደንቦች (ሴራ) ከመንግስት ህግጋት ጎን ለጎን በህዝብ መልካም አስተዳደር እና በግጭት አፈታት ረገድ ጠቃሚ ነው፡፡
የጎርደና ሴራ
ማለት እጅግ ጽኑና ጠንካራ በመሆኑ ሁሉም የሶዶ ክስታኔ ቤተ-ጎራጌ ማህበረሰብ በእኩል ደረጃ የሚታይበት ባህላዊ ፍትህ የሚሰጥበት ሥርዓት ነው፡፡ እንዲሁም እያንዳንዱ ሰው በሶዶ ጎርደና ሴራ ፊት እኩል የመሰማትና ፍትህ የማግኘት መብቱ ስላለው ያለምንም ልዩነት ትክክለኛ ፍትህ የሚያገኝበት ባህላዊ አስተዳደራዊ ስርዓት ነው፡፡ የጎርደና ሴራም በሶዶ ክስታኔ ቤተ-ጎራጌ ማህበረሰብ ዘንድ ከብዙ ዘመናት በፊት ጀምሮ ማንኛውም ዓይነት ፍትህ የሚጠይቁ ጉዳዮች ማህበራዊም ሆነ ኢኮኖሚያዊ ችግሮቻቸውን የሚፈቱበት ስለሆነ በማህበረሰቡ ዘንድ ተቀባይነት ያለው ነው፡፡
ዳኝነት በጎርደና ሴራ
በጎርደና ሴራ መሰረት ሲተዳደር የኖረው የሶዶ የክስታኔ ቤተ-ጉራጌ ህዝብ በህብረተሰቡ ውስጥ ውንብድና፤ መዘራረፍን፤ መጠቃቃትን ወዘተ… እናዳይኖር ቀደም ሲል በየደረጃወ ወይም በየዘርፉ በህግ የተመደቡ ዳኞች ነበሩ ፡፡እንዚህም ዳኞች የስራ መደባቸው የአንዱ ከሌላው የተለየ ሲሆን የዳኞች የስራ ስያሜ እና ተግባር እነደሚከተለው በዝርዝር ቀርቧል
“የዎዳቦ ዳኛ”፡- ማለት መሬት ለሌለው ሰው በገመድ እየሰፈረ የሚያደላድልና በመሬት እና ድንበር ጉዳዮችም ግጭት ሲከሰት በዳኝነት የሚገላግል ነበር ፡፡
“የጉፍ ዳኛ”፡- ማለት (ከሸክላ የተሰራ በእለተ ሰንበቱ ፀበል / ጠላ እየተሞላበት የሚዘከርበት ጽዋ/ ገንቦ ነው) የቤተክርስቲያን አስተዳደር በስርዓት እዲመራ፣ ምእመናንን አስራት በኩራት በወቅቱና በአግባቡ እንዲከፍሉ ፣የካህናትና የዐቃቢት ዓመታዊ ደሞዝ ምእመናን በነፍስ ወከፍ እያወጡ ማስከፈልንና የሰንብትን ቀን ማስከበር የጉፍ ዳኛ የስራ ድርሻ ነበር ፡፡
“የደቆት ዳኛ” (ደኦት)፡- ማለት ጥሬ ትርጉሙ መቀነት ሲሆን የደቆት ዳኛ ጋብቻ ጉዳይ ላይ ይካተታል፡፡ ይህንንም ማለት በሁለት ተቃራኒ ጾታዎች መካከል ጋብቻ ሲፈጸም ጋብቻው ህጋዊነት የሚኖረው ከሲምቢታ ጎሳ የደቆት ዳኛ እንደህግ አስፈጻሚ በሚገኝበት አግባብ ነው ያለበለዚያ በተለይም በቀድሞ ጊዜ ያለ ዳኛው እውቅና የሚፈጸም ጋብቻ ህጋዊ ተፈጻሚነት አልነበረውም ስለሆነም የደቆት ዳኛው በልጅቷ ቤተሰብ ቤት በፍጥምጥሙ እለት በመገኘት ወላጅ አባት እና እናት ሴት ለጃቸውን ወደው እና ፈቅደው ለባል መስጠታቸውን በደቆት ዳኛው አማካኝነት ስመ እግዚያብሄርን በማስጠራት ይረጋገጥ ነበር ፡፡ ይህ ሁኔታ ዛሬም ቢሆን በተለያዩ የገጠሩ ክፈሎች ያለ ነው፡፡
“የጉዳ ዳኛ” ፡- ጉዳ ማለት በመሀላ ወይም በቃል ኪዳን የሚፈጸም የሁለት ተቃራኒ ወገኖች የማስታረቅ ስራ ነው፡፡
“የጡር ዳኛ” ፡- ማለት የሳቡኘት /የእድር ዳኛ ሲሆን በአንድ ሳቡኘት /እድር ወስጥ የሚገኙ የማህበረሰብ አባላት በሙሉ በጎርደና ሴራ መሰርት ስርዓት አክበረው እና ተግባብተው እንዲኖሩ ይቆጣጠራል ይህም ማለት በዳይና ተበዳይ ሲኖር ተከታትሎ በአግባቡ ያካክሳል ፡፡
“የሞጨ ዳኛ” ፡- ሞጨ ማለት መንግድ ሲሆን በክስታኔ ጉራጌ ማህበረሰብ ውስጥ አምስት አይነት መንገዶች አሉ ሲሆን እነዚህም፡-
ሀ. ውር ሞጨ፡- ማለት አውራ ጎዳና ማለት ሲሆን እነዚህ ጎዳናዎች ረጃጅምና ከሀገር ሀገር የሚያገናኙ ናቸው፡፡
ለ. የአገር ሞጨ፡- አገር ሲባል እዚያው በሶዶ በክስታኔ ቤተ-ጉራጌ ውስጥ የሚገኙ 22 አገሮች ሲሆኑ እነዚህ አገሮች ሁሉም በሚባል መልኩ የሚገናኙበት የእግር መንገዶች ያሏቸው ሲሆን እንደሚታወቀው አንዳንድ ቀና ሰዎች የመኖራቸውን ያህል ሌሎች ተንኮለኞች እና ስግብግብ ሰዎች የህዝብ መመላለሻ መንገዶች እያጠበቡ ለግብርና ስራ እንዳያውሉ የሚቆጣጠረው ወይም የሚከላከለው የሞጨ ዳኛ ነው፡፡
ሐ. የአርባ ሞጨ፡- ማለት በጣም ሰፊ የሆነና ሰዎች ከመንደር አስክሬን ተሸክመውበት ወደ ቤተክርስቲያን የሚሄዱበት መንገድ ነው፡፡
መ. የቀንበረ ሞጨ፡- ማለት ሰዎች በሬ ጠምደው ወይም ከብቶች ነድተው ከመንደራቸው ወደ ስምሪት የሚሄዱበት መጠነኛ ስፋት ያለው መንገድ ነው፡፡
ሠ. የእግር ሞጨ፡- ማለት በሁለት ግለሰቦች መሬት /ይዞታ መካከል ሚገኝ የእግር መንገድ ነው፡፡
መስቀል በዓል በምስራቅ ጉራጌ

መስቀል በዓል በምስራቅ ጉራጌ ማህበረሰብ ዘንድ ትልቅ ቦታ የሚሰጠውና ሰፊ ቅድመ ዝግጅት ተደርጎበት የሚከበር በዓል ነው፡፡ የመስቀል በዓል ዝግጅት የሚጀምረው መስቀል በተከበረበት ዓመት በዓሉ እንደተጠናቀቀ ለሚቀጥለው ዓመት የመስቀል በዓል ማሰብ ይጀመራል፡፡ በተለይ ከትውልድ ቀዬያቸው ርቀው የሚኖሩ ተወላጆች ከቀን ሰራተኛው እስከ ደመወዝተኛው ከሱቅ በደረቴ እስከ ትልቁ ነጋዴ ለመስቀል በዓል ብለው ከበጋው ወራቶች ጀምሮ የተለየ ገንዘብ በየጊዜው ጣል በማድረግ ያጠራቅማሉ፡፡ እናቶችም ዓመቱን ሙሉ የማያቋርጥ የቅቤ ውጆ /የቅቤ እቁብ/ እያጠራቀሙ ለበዓሉ ዝግጅት ያደርጋሉ፡፡
በዓሉ ሶስትና አራት ወራት ሲቀሩት ዝግጅቱ እየተጧጧፈ ይሄዳል፡፡ በዚህ ወቅት የስራ ክፍፍሉ በእድሜና በፆታ ተደላድሎ ለሁሉም እንደ አቅሙና ችሎታው ይሰጣል፡፡ ወጣት ወንዶች ለመስቀል በዓል የሚሆን እርጥብ አንጨት ከጫካ ፈልጎ መፍለጥ፣ መከመርና ማደራረቅ ከደረቀም በኋላ ቤት አስገብቶ ቆጥ ላይ መደርደር ሲሆን፣ የአባውራዎች ድርሻ የሚሆነው ለእርድ የሚቀርቡ ከብቶች ማድለብና ማዘጋጀት ከቤት ከሌለም አስቀድሞ ገዝቶ ማድለብ እንዲሁም በመስቀል ወቅት በቤት ውስጥ ያሉት ከብቶች የሚሰማሩበት ክልክል የሳር ቦታ (ኩትር) መከለልና ለተወሰኑ ቀናቶች የሚሆን ሳር አጭዶ ማቆየት እና ለበዓሉ የሚሆኑ ቢላዎች መግዛት ማስሞረድ የመሳሰሉት ናቸው፡፡
የወጣት ሴቶች የስራ ድርሻ ደግሞ ቤት ማሳመር የተለያየ ቀለም ባላቸው አፈሮች ቤት መቀባት ሲሆን እማውራዎች በቅድሚያ እንሰት ፍቀው ማዘጋጀት በደቦ አዲስ ጅባ መስራት ወይም መግዛት፣ ያረጁና ያለቁ የቤት ቁሳቁሶች በአዲስ መለወጥ፤ ለበዓሉ የሚሆን ሚጥሚጣ ማዘጋጀት፤ ፈሳሹ ተንጠፍጥፎ የወጣለት የበዓል ቅቤ በተለያዩ ቅመሞች አሽቶ ማንጠርና ለበዓል የሚሆኑ ባህላዊ መጠጦችን ማዘጋጀት ዋና ዋና ተግባራት ናቸው፡፡
ከነሀሴ 12 ጀምሮ ደመራ ይደመራል ሌሎች ቅደመ ዝግጅት የሚፈልጉ ስራዎች በትጋትና በንቃት ይከናወናሉ፡፡
በዓሉ ሰፊ ቅድመ ዝግጅት ከተደረገበት በኋላ ከመስከረም 12 እስከ ጥቅምት 5 ድረስ ለበዓሉ ተብሎ የተዘጋጁ ምግቦችና መጠጦች እየተጠቀሙ በታላቅ ደስታና ጭፈራ እንዲሁም በህዝቡ ማህበራዊ ህይወት ውስጥ ልዩ ልዩ ክንዋኔዎችን በማከናወን የሚከበር ሲሆን የቀናቶቹ ስያሜና የሚከናወኑት ተግባራት ቀጥለን እንመለከታለን፡፡
መስከረም 12 ሌማት ያወርድቦ ማይ/መሶብ የሚወርድበት ቀን/ የሚባል ሲሆን ለምግብም ሆነ ለመጠጥ ማቅረቢያነት የሚውሉ ቁሳቁሶች ከየግርግዳውና ከተሰቀሉበት ስፍራ ሁሉ ይወርዱና በጥንቃቄ ታጥበውና ፀድተው እስከ ጥቅምት 5 ድረስ ለምግብ ማቅረቢያነት አገልግሎት የሚቆዩ ይሆናል፡፡ እንዲሁም ሁሉም ቤቱን አጽድቶና አዳዲስ ጅባዎች አነጣጥፎ ለመብላት ዝግጅት የሚጠናቀቅበት እለት ነው፡፡
መስከረም 13 ይህ እለት "ዎልቀነ/ወሬት የኸና" የሚባል ሲሆን በዚህ ቀን ሴቶች የመስቀል በዓል ዝግጅታቸውን አጠናቀው ለመስቀል ተብሎ በተዘጋጀው በሁሉም የምግብ አይነቶች ላይ ሙከራ ስለሚደረግ ሴቶች የሚጠግቡበትና ልጆች እንቅልፍ የሚያጡበት ቀን ነው ተብሎ ይታሰባል፡፡ ለዚህም የራሳቸው የሆነ የስንኝ ቋጠሮ አላቸው፡፡
ዎል ቀነ ዎል ቀነ
ምሽት ይገራቦ ቀነ
ታምብል ይጋም ኮነ በማለት በስነ-ቃል ይዜምለታል
መስከረም 14 ‹‹ደንጌሳት/ይፍት›› በመባል የሚጠራ ሲሆን በእለቱ ለሁሉም የቤተሰብ አባል በተዘጋጀለት የሸክላ ጣባ ‹‹ደንጋሳ›› የጎመን ክትፎ የሚበላበት ቀን ነው፡፡ በዚህ እለት ማታ ሁሉም በየደጃፉ ትንንሽ ዳመራ የሚያቃጥል ሲሆን ይህም ‹‹የባዮች ምጅር/የዴንጋ ሙኪር›› ይባላል፡፡ ዳመራው በሚለኮስበት ወቅት ሁሉም በየደጃፉ ከየአድማሱ የሚቃጠለውን ዳመራ ለማየት ለዚህ እለት ላደረስከን ተመስገን እንደማለት ሴቶች እልልታ ያሰማሉ፡፡
መስከረም 15 ‹‹ጨርቆስ ወይም የእርድ ማይ/ወኸሚያ›› የሚባል ሲሆን ይህ ቀን ዋናው የመስቀል በዓል የሚከበርበት እለት ነው፡፡ በእለቱም የአባዎራዎች ተግባር ጎልቶ የሚታይበት ሆኖ እያንዳንዱ የቤተሰብ አባል ሁለትና ከዚያ በላይ በመሆን የደለበ ሰንጋ የሚታረድበት እለት ነው፡፡ የታረደው ከብት ስጋ ተበልቶ ወደ ቤት እንደገባ ቤተሰቡ ይሰበሰብና ስጋውን ጎረድ ጎረድ በማድረግ በቅድሚያ ‹‹ጨፉየ›› በቂቤ ተነክሮ ቢበላ ከቆይታ በኋላ አመሻሽ ላይ ሲዘጋጅ የቆየው ክትፎ በአልባብጫት/ቆጮ/ ቀርቦ ይበላል፡፡ በዚህ ቀን አባወራው ያረደው ስጋ ድንገት ጉፋያ ከሆነ ሴቶቹ በግጥም ይሳደባሉ፡፡
ጬሮደም ኧጭንን
ቅብዲም ነስጭንን
ዬመናጊ ጠብጠት
ንቶናም በጨበር
መልክኛ ንዥንን፡፡
የዚህ ስንኝ ትርጓሜ አባወራው ያረደው ስጋ ጮማ ያለመሆኑ የሚገልፅና ለመስቀል በዓል በቂ ዝግጅት እንዳላደረገ የሚያመለክት ሲሆን ሴቷ በቂ ዝግጅት ማድረጓን ለመግለፅ አንተም ያረድከው ጉፋያ ብላና እኔም ያዘጋጀሁት ቅቤ ልጠጣና ፀሐይ ላይ ተቀምጠን ፊታችን ይታይ እንደ ማለት ነው፡፡ በእርድ ቀን ቤተሰቦቹ ዘንድ ሳይደርስ በነበረበት ከተማ ለቀረ አባውራ እማውራዋ እንዲህ እያለች ግጥም ታሰማለች
በርበሬም ዎቀጥኩም
ጥወም አክላለትኩም
አምብልም አረጥኩም
ጉንስም አልባበጥኩም
አናቀርብሆም
ዬጌ አቢ ቀበጥኩም፡፡
ትርጉሙም በርበሬ፣ ቅቤ፣ ጎመን፣ ቆጮም አዘጋጅቼአለሁ አቅርቦ ለመብላት ግን አባውራው ቀርቶብኛል፡፡
አክራሚ ይዎሉም
ይሰላው መስቀለ
አደራ ዬኩንከ
በሚዳ አትዋለ፡፡
ይህ ግጥም አባዎራው ውጭ እንዳይውል የእማዎራዋ አደራ ሲሆን ትርጓሜውም ከእንቁጣጣሽ ቀጥሎ የሚመጣው መስቀል ነውና አደራህን ውጭ አታሳልፍ ማለት ነው፡፡
መስከረም 16 የአባንዳ እሳት/የጉርዝ ምጅር/ የአባቶች ትልቁ ዳመራ የሚቃጠልበት እለት ሲሆን ወጣት ወንዶችና ሴቶች ቤተክርስቲያን ሄዴው የሚጨፍሩበትና ሃይማኖታዊ ስርዓት የተከተለ ዳመራ የሚቃጠልበት ቀን ነው፡፡ ከቤተክርስቲያን መልስ ሁሉም የቤተሰብ አባል በየጣባው የተዘጋጀለትን ክትፎ ወዳጅ ጓደኛውን እየጠራ በየተራ ይገባበዛል፡፡
መስከረም 17 በማህበረሰቡ አጠራር ‹‹ንቅባር›› ‹‹ማለቅ በዓል›› ወይም ትልቅ በዓል ‹‹የከሰል ማይ›› ወይም የከሰል ቀን ተብሎ ይታወቃል፡፡
ከመስከረም 17- መስከረም 23 ያለው ጊዜ የሙሽሪት ወላጆች ወይም የሙሽሪት አማቶች የመጠየቂያ ጊዜ ሲሆን የጀወጀ/የጀወቸ/ ይባላል፡፡ ሴት ልጆች የጀወጀ ሲሄዱ ለእናቶቻቸው የፀጉር ቅቤ ሻሽና መቀነት ለአባቶቻቸው ባርኔጣ፣ ጭራና ጋቢ ሲይዙ ባሎቻቸው ደግሞ ዘመናዊ መጠጥ፣ ሙክትና ገንዘብ በመያዝ ይሄዳሉ፡፡ ከሙሽሪት ወላጆች ቤት እንደደረሱ የያዙትን ስጦታ በጎረቤት ፊት ካስረከቡ በኋላ የቤተሰቡ አንጋፋ መርቀው ሲያሳርጉ ሙሽሪትና ሙሽራው ለትልልቁ ግምባር ግምባሩን ለሌላው ጎንጩን በመሳም ቡራኬ ተቀብለው ይቀመጣሉ፡፡ ይህም በወላጆቻቸው ዘንድ ትልቅ ሞገስና ክብር ሲያሰጣቸው የመስቀል በዓሉ ፌሽታና ደስታ ድርብ ያደርገዋል፡፡
መስከረም 18 ‹‹የፊቃቆ ማይ››/የስንደዶ ለቀማ ቀን/ ተብሎ ይጠራል፡፡ የየመንደሩ ልጃገረዶች ስንደዶ ለቀማ የሚሰማሩበት ቀን ሲሆን በልጃገረዶች ዘንድ ትልቅ ቀን ሆኖ ለሚቀጥለው መስቀል በዓል የተለያዩ የስፌት ጌጦችን እንደ መሶብ እና ሌሎች ከስፌት የሚሰሩ የመገልገያ እቃዎች ለመስፋት የሚዘጋጁበት እለት ነው፡፡
ከመስከረም 16 ጀምሮ እስከ ጥቅምት 5 ድረስ በሚቆየው የአዳብና ባህላዊ ጨዋታ በተለያዩ ስፍራዎች በሚኖረው የዘፈንና ጭፈራ ትዕይንቶች በመሳተፍ ወጣት ወንጆችና ሴቶች ከልብ በሆነ የደስታ ስሜት ተውጠው ሎሚ፣ ብርቱካን፣ ከረሜላ፣ ሸንኮራ አገዳ በመለዋወጥ እጮኛ የሚመርጡበት በዓል መሆኑ እና እንደ ቤተሰብና እንደ አካባቢ በአዲስ ዓመት የሚሰሩ ስራዎች ተለይተው እንዴት መሰራት እንዳለባቸው የሚመከርበት የሚታቀድበት መሆኑ የመስቀልን ማህበራዊ ፋይዳ እጅግ ያጎላዋል፡፡