የሀላባ ተፈጥሯዊ መስህቦች
የሀላባ ተፈጥሯዊ መስህቦች
አርቶ ፍል ውሃ
የሀላባ ዞን የተለያዩ ተፈጥሮአዊና ባህላዊ እንዲሁም ሰው ሰራሽ የሆኑ መስህቦች ባለቤት ናት፡፡ ዞኑ ከመዲናችን አዲስ አበባ በሻሸመኔ 313 ኪ/ሜትር እንዲሁም በቡታጅራ 245 ኪ/ሜትር ርቀት ላይ ሲገኝ ከክልላችን መዲና ሆሳዕና ከተማ ደግሞ በ80 ኪ/ሜትር ርቀት ላይ ይገኛል፡፡ስለ ሀላባ ዞን በጥቂት እንዲህ ካስተዋወቅናቹ በውስጧ ስለሚገኙት በርካታ ተፈጥሮአዊና ባህላዊ እንዲሁም ሰው ሰራሽ መስህቦች መካከል ተፈጥሮአዊ በሆነው የአርቶ ፍል ውሃ ላይ በማተኮር በውስጡ ያሉትን ድንቅ መረጃ እናሳውቆታለን፡፡
የአርቶ ፍል ውሃ የሚገኘው በአርሾ ቀበሌ ገበሬ ማህበር ውስጥ ሲሆን ከሀላባ ዞን ዋና ከተማ ቁሊቶ በ10 ኪ/ሜትር ርቀት ላይ ይገኛል፡፡ ይህን ተፈጥሮአዊ መስህብ ከሌሎች መስህቦች ልዩ የሚያደርገው በርካታ ባህርያት ያሉት መሆኑ ድንቅ አድርጎታል፡፡ ይህ ፍል ውሃ ለብርድ፣ ለቁርጥማት ለተለያዩ ሰውነት ላይ ለሚወጡ ቁስሎችና ለሌሎችም ከጤና ጋር ለተያያዙ ጉዳዮች ወዘተ ፍቱን መድኃኒት መሆኑ በአብዛኛው ጎቢኝዎች ዘንድ የተመሠከረለት በመሆኑ ልዩ ያደርገዋል፡፡ የአርቶ ፍል ውሃ ሌላው አስደናቂ ነገር ከፍል ውሃው ላይ የተለያዩ ሰብሎች ማለትም እንደ በቆሎ እሸትና የተለያዩ የጥራጥሬ ሰብሎችን በፍል ውሃው ውስጥ በዕቃ/በገመድ በማሰር በሚጨመርበት ወቅት 15 ደቂቃ በማይሞላ ጊዜ ቶሎ በማብሰል የሚታወቅ ነው፡፡ እንዲሁም በአከባቢው ለጉብኝት የመጡ ቱሪስቶች ሻይንና ቡናን ለመጠጣት ቢፈልጉ እንኳን የፍል ውሃውን በማንቆርቆሪያ በመቅዳት/በመጨመር/የተፈጨ ቡና ወይም ሻይ ቅጠልና ስኳር በመጨመር ማፍላት ሳይጠበቅባቸው በዚህ ድንቅ የተፈጥሮ መስህብ መጠቀም መቻላቸው ደግሞ ልዩ ያደርገዋል፡፡በዚህ መስህብ አከባቢ በፍል ውሃው ለመጠቀም የሚመጣ ጎብኚ በፍል ውሃው ከመታጠቡ ባሻገር በተፈጥሮአዊ ይዘቱ በሚለቀው እንፋሎት በመታጠን የሚያገኘው እርካታ ይበልጥ አስደናቂ አድርጎታል፡፡የአርቶ ፍል ውሃ በውስጣዊ እምቅ ሃይሉና በተፈጥሮአዊ ይዘቱ በመታገዝ ወደ ላይ ከ9 እስከ 12 ሜትር ከፍታ ሲዘል ላየው ምን ያህል አስደሳች እንደሆነ መናገር አያዳግትም፡፡ከዚህም በተጨማሪ ይህ ፍል ውሃ ለሰዎች ከሚሰጠው ፈዋሽ መድኃኒትነቱ ባሻገር ለከብቶችም በማጠጣትና አሞሌ ጨውን አብሮ በማብላት ለጤንነታቸው ትልቅ ሚና ያለው ፍል ውሃ ነው፡፡ ከዚህ ጋር በተያያዘ ይህን ፍል ውሃ ከተለያዩ የአጎራባች አከባቢዎችና የሀገሪቱ ክፍሎች እንዲሁም ከዞኑ በየወቅቱ የሚጎበኙት ቱሪስቶች ቁጥር ከፍተኛ ነው፡፡
የጎቶ ፏፏቴ
የጎቶ ፏፏቴ ተፈጥሮአዊ በሆነው የዲጆ ወንዝን ተከትሎ የተፈጠረ ፏፏቴ ሲሆን የጎቶ ፏፏቴ ደግሞ የሚገኘው በዌይራ ዲጆ ወረዳ በአለኬ ጌሮ ቀበሌ በጎቶ ንዑስ የሚገኝ መስህብ ነው፡፡የጎቶ ፏፏቴ ከሀገሪቱ መዲና አዲስ አበባ በ321 ኪ/ሜትር ከማዕከላዊ ክልል ርዕሰ ከተማ ሆሳዕና በ156 ኪ/ሜትር የሚገኝ ሲሆን ከዞኑ ዋና ከተማ ቁሊቶ ደግሞ በ76 ኪ/ሜትር ርቀት ላይ የሚገኝ መስህብ ነው፡፡የመስህቡን አፈጣጠር በተመለከተ ይህች ምድር በተፈጠረች ጊዜ አብሮ የተፈጠረ ተፈጥሮአዊ መስህብ ሲሆን ወደ መስህቡ የሚወስድ መንገድ ያለው ቢሆንም ቀሪ የመንገድ ስራዎች ለቱሪስቱ ምቹ ማድረግ ያስፈልጋል፡፡በጎቶ ፏፏቴ መስህብ ዙርያ ያለውን ውብና ማራኪ ሁኔታን ስንመለከት በመስህቡ አካባቢ የተለያዩ አይነት ዝርያ ያላቸው የተፈጥሮ እዕጽዋቶችና የተለያዩ የዱር እንሰሳትን በቀላሉ መመልከት የተለመደና መንፈስን የሚያድስ የአየር ሁኔታ የተላበሰ መስህብ መሆኑ ድንቅ አድርጎታል፡፡በዚህ መስህብ ዙርያ ተፈጥሮ ያስቀመጠችው ሌላው ውብ ነገር ፏፏቴው ከላይ ወደ ታች ሲምዘገዘገው ለሚያየው ከ120 ሜትር ከፍታ ላይ መሆኑ ደግሞ የፏፏቴውን ውበት ልዩ እንዲሆንና ለቱሪስቱ እይታ ሌላው ሳቢ ገጽታ ነው፡፡በሌላ በኩል የተፈጥሮ ጉዳይ ተነግሮ የማያልቅ ከመሆኑም ጋር በተያያዘ በዚህ ፏፏቴ ዙሪያ ሌላው ድንቅ የሆነው በተፈጥሮ የተቀመጡ እጅግ በጣም ትላልቅ እንደ አውልት የቆሙ ብዛታቸው ከ80 በላይ የሆኑ የተፈጥሮ አለቶች/ድንጋዮችን/በመስህቡ ዙሪያ መኖሩ ደግሞ ለፏፏቴው ውበት ተጨማሪ ገጽታዎች መሆናቸው መስህቡን ልዩ አድርጎታል፡፡የጎቶ ፏፏቴ በአላጌ አንባ አካባቢ በቅርበት የሚዋሰን ከመሆኑ ጋር በተለይም በአላጌ አንባ ውስጥ የተለያዩ የመንደር ስያሜዎች ያሉ በመሆኑ የጎቶን ፏፏቴ ቲንሽ አለፍ እንዳሉ በአላጌ አንባ ውስጥ በኩባ ሰፈር የሚገኘውን የመዝናኛ ስፍራ በቅርበት ማግኘት መቻሉ ደግሞ ይህን መስህብ ለመጎብኘት ምቹ ሁኔታን የሚፈጥር መስህብ መሆኑ ደግሞ የመጎብኘት ፍላጎትን የሚጨምር ነው፡፡ሌላው በዚሁ መስህብ ዙርያ ከመዝናኛው ባሻገር የአላጌ አንባ ዋና የችግኝ ጣቢያ መገኛ መኖሩ ይበልጥ ሌሎች ተጨማሪ የመጎብኘት ሁኔታዎችን የሚያሰፉና ውስጥን የሚያስደስት እንዲሁም የሚስብ ቦታ መሆኑ ድንቅ ያደርገዋል፡፡
የስፋሜ ዋሻ
የሚገኘው በአይመሌና በሀቢቦ የገጠር ቀበሌ ውስጥ ነው፡፡ዋሻው ከዞኑ ዋና ከተማ ቁሊቶ በ14 ኪ/ሜ ርቀት ላይ ይገኛል፡፡ የስፋሜ ዋሻ ስያሜውን ያገኘው ከአከባቢው ህብረተሰብ ሲሆን በድሮ ጊዜ ሰዎች ቦታውን ለመደበቂያነት ወይም ከጠላት ለመሸሸጊያነት እንደተሰራ የሀገር ሽማግሌዎች ይናገራሉ፡፡ስፍሜ ዋሻ የተቆርቆርበት በ1930ዓ/ም በወቅቱ በነበርው ጦረኛ ቦያሞ ባቢሶ አማካኝነት እንደሆነ የታሪከ መረጃ ያመላክታል፡፡ቦያሞ የወሸርመኔ ጎሳ ቤተሰብ አካል ሲሆን በወቅቱ በአካባቢው ከመጣው ወራሪው አካል ጋር ውግያ ለመግጠም ዋሻውን በማዘጋጀትና ለመሸሸጊያነት ለመጠቀም እንደተሰራ የታሪክ መረጃ ያመለክታል፡፡ ወጣቶቹ ከወራሪ ጠላት ጋር ውግያ ገጥሞ እስኪመለሱ ድረስ ህፃናትና አዛውንቶች በዋሻው ውስጥ ገብተው ይቆያሉ፡፡ ጦረኞቹ ድል አድርገው ወደ መንደራቸው ሲመለሱ መተናከል ውጡ ብለው ድምፅ ያሰማሉ፡፡በውስጡም ያሉ ሰዎች ድል አድርገው የመጡትን ወገኖቻቸውን ከዋሻው በመውጣት ይገናኛሉ፡፡ዋሻው በውስጡ በርካታ የጀግንነት ገድል የያዘና ታሪካዊ የሆነ የእጅ ጥበብ ያረፈበት እድሜ ጠገብ የሆነ ዘመን የማይሽረው በብዛትም ከ30 በላይ የሆኑ ዋሻዎችን በውስጡ ይዞ ይገኛል፡፡ሲፍሜ ማለት ሁሉ ተስማሚ፣ለጤና አመቺ የሚል ትርጉም ያለው ነው፡፡ሲፍሜ ዋሻ አካባቢ በስተደቡብ የሀላባ ዞን ዋና ከተማ ሀላባ ቁሊቶን ሙሉ ገጸታዋን ከቦታው ሆኖ መመልከት ይቻላል፡፡በተለይም አመሻሽ ላይ ሆነው ሲመለከቱ በቁሊቶ ከተማ ድምቀት የሆኑት መስጂዶችን በርቀት ሲመለከቱ የሀላባ ቁሊቶ ውበትና ሳቢ ገጽታን መመልከት ይቻላል፡፡ ዋሻው የተሰራበት ዋና ዓለማ በአከባቢው በተለያዩ ዘመናት የድንበር ግጭቶችና አለመግባባቶች ስለሚከሰቱ የአከባቢው ማህበረሰብ በተለይም ሴቶችና ህፃናት እነዲሁም ደግሞ ከብቶቻቻውን ለመሸሸግ እንደሰሩት መረጃዎች ያመለክታሉዋሻውን አስገራሚ የሚያደርገው በውስጡ ብዙ ሰዎችን በአንድ ጊዜ መያዙና ውስጡ ላይ ምሶሶ ያለው መሆኑ አስደናቂ ያደርገዋል፡፡ በአከባቢው በተለያዩ ቦታዎች ላይ ዋሻው መኖሩ ውበቱን አጎልቶታል ፡፡
የተፈጥሮ ድልድይ (ሆካሜ)

የሀላባ ዞን የተለያዩ በተፈጥሮዊና ባህላዊ ሰው ሰራሽ የሆኑ መስህቦች ባለቤት ናት፡፡ ተፈጥሯዊ ከሆኑት መስህቦቻችን ውስጥ የአርቶ ፍል ውሃ የደነቤ ፋማ ፋፋቴ፣የጎልጆ ተራራ ደንና የተፈጥሮ ድልድይ ይጠቀሳሉ፡፡ከዚህ በመቀጠል ላወጋችሁ የፈለኩት በሀላባ ዞን በዌይራ ዲጆ ወረዳ በአንሸኮራ ቦጢ ቀበሌ የሚገኘውንና ከዞኑ ከተማ ቁሊቶ በ65ኪ/ሜ ርቀት ላይ ስለሚገኘው መስህብ ይሆናል፡፡ የድልድዩን አፈጣጠር ስንመለከት ተፈጥሮ በተፈጥሮአዊ አደጋ ክስትተ/natural disaster/ ማለትም በጎርፍ ክስተት የተፈጠረ መሆኑን የአካባቢው ሽማግሌዎችና አዋቂዎች ይናገራሉ፡፡ መረጃዎች እደሚጠቁሙት ከሆነ ከብዙ ዘመናት በፊት በክረምት ወቅት በሚመላለሰው ጎርፍ አማካኝነት የተፈጠር መሆኑን ይናገራሉ፡፡ የድልድዩ ይዘት ልዩ የሚያደርገው ለሰው ሰራሽ ድልድይ እንደምንጠቀመው አይነት ግንባታ ነው፡፡ የተለያዩ ቁሳቁሶችና ግንባታዎችን በመጠቀም ያልተሰራ በመሆኑ ድልድዩን እጅግ አስደናቂና ማራኪ ያደርገዋል፡፡ ሌላው ለየት የሚያደርገው የአካባቢው ነዋሪዎች ለዘመናት እንደ መሸጋገርያነት ቢጠቀሙትም እስከ አሁን ድረስ ጥገና ሳያስፈልገው እያገለገለ መሆኑንና በቀበሌዎቹ መካከል እስካሁን ድረስ የሚያገናኝ ብቸኛ ድልድይ መሆኑ ነው፡፡ ከድልድዩ ጎን ለጎን የሚገኘው ሸለቆ ጥልቀት በአይን ለመመልከት የሚያዳግት ሲሆን ከዚህኛው ድልድይ በስተግራበ 1 ኪ.ሜ ርቀት ላይ ተመሳሳይነት ያለው ሁለተኛው የተፈጥሮ ድልድይ ይገኛል፡፡ በዚህ ጽሁፍ ላይ ከዘረዘርናቸው ውጭ አካባቢውን ለመጎብኘት የሚጡ ጎብኝዎች አስደናቂ እና አይንን የሚስብ የተፈጥሮና የመሬት አቀማመጥ፣የአብያታና የሻላ ሀይቆችና ፓርኮች መገኛ አካባቢ እዲሁም አስደናቂው ሰንሰለታማ የጎልጆ ተራራ ደን መገኛ ስፈራ በመሆኑ ወደ አካባቢው መተው ለሚዝናኑ ጎብኚዎች የአዕምሮ እርካታና መልካም የሆነ ጊዜን አደሚያሳልፉ ምንም ጥርጥር የለንም፡፡
የአሶሬ ጥብቅ ደን

የሀላባ ዞን የተለያዩ ተፈጥሯዊ፣ ባህላዊ፣ታሪካዊና ሰው ሰራሽ መስህብ ባለቤት ናት፡፡ ከዚህ ውስጥ ሰው ሰራሽ የመስህብ ሀብታችን የሆነው የአሶሬ ጥብቅ ደን የሚገኝ ሲሆን ይህ ደን ከዞኑ ዋና ከተማ ቁሊቶ በ12ኪ/ሜትር ርቀት ላይ ይገኛል፡፡ የአሶሬ ጥብቅ ደን 125 ሄክታር ቦታን የሚሸፍን ሲሆን ደኑን በአከባቢው ከሚያዋስኑት ቀበሌያት በሰሜን የአሶሬ ቀበሌ፣በደቡብ የብላቴ ወንዝ፣በምስራቅ አሾካ ቀበሌ፣በምዕራብ ሸቃጤ ቀበሌ ያዋስኗታል፡፡ ደኑ በደርግ ዘመነ-መንግስት የነበረ ቢሆንም በወቅቱ በነበረው የደን ጭፍጨፋ መመናመን ያጋጠመው ቢሆንም እንኳን የመንግስት ልማት ፖሊሲ መሠረት በ1986 ዓ/ም መልሶ በመትከል እስከ ዛሬ ድረስ ተጠብቆና ለምቶ በመኖሩ ዛሬ ላይ ጥቅጥቅ ብሎ ለተለያዩ የዱር እንሰሳቶች መጠለያ በመሆኑ ለሰውና ለሌሎችም እንስሳቶች የጎላ ጠቀሜታ በመስጠት ላይ ይገኛል፡፡ ከደኑ የተለየ ውበት ጋር ተያይዞ ከግርጌው የሚፈሰው የብላቴ ወንዝ ጋር ተደምሮ ለሚመለከተው ጎብኚ ልዩ የሆነ አድናቆትን ይጨምርበታል፡፡
በሌላ መልኩ በደኑ ውስጥ ድንቅ የሆኑ የዱር አራዊቶች ያሉ ሲሆን ከእነዚህ ውስጥ የከርከሮ፣ የጅብ፣ የጃርት፣ ጥንቸል እና ሌሎችም አራዊቶች ይገኛሉ፡፡ ከእፅዋት ዝርያ አኳያ የተለያዩ የእፅዋት ዝርያዎች ይገኛሉ፡፡ በአጠቃላይ የደኑን ሀብቶች ተንከባክቦ ከመጠበቅ አንፃር ከተለያዩ ህገወጥ ሰፈራ፣የግጦሽ ስምሪት፣የእንሳስት አደን፣የእሳት ቃጠሎ እንዲሁም የደን ምንጣሮ አደጋዎችን በመከላከል የገቢ ምንጭ የሚያስገኝበትን ሁኔታ ለማመቻቸት እየሰራን እንገኛለን፡፡ የአሶሬ ደን የኢኮ-ቱሪዝም ሴንተር ሆኖ እንዲያገለግል በክልል ደረጃ የተመረጠ ስለሆነ ለቀጣዩ ሰፊ ስራዎችን አጠናክረን መስራት ይጠበቅብናል፡፡
ደነቤ ፍማ ፏፏቴ

ተፈጥሮ የሰጠችን ሀብት የሰው ልጅ ከሚሰራቸው ስራዎች በላይ እጅጉን የሚያስደንቀውና የሚማረከው የተፈጥሮ ሀብት መሆኑ ሁላችንንም በአንድ ቃል የሚያስማማን ሀቅ ነው፡፡በመሆኑም ያለንን የተፈጥሮ ጸጋ በዘላቂነት በማልማትና በመጠበቅ ለትውልድ ከማስተላለፍ ባለፈ ከዘርፉ የሚገኘውን ገቢ ማሳደግ ይኖርብናል፡፡ከዚህ ጋር በተያያዘ የሀላባ ዞን በርካታ ባህላዊ፤ታሪካዊና ሰው ሰራሽ እንዲሁም ተፈጥሮዊ መስህቦች ባለቤት ናት፡፡የሀላባዞንበማዕከላዊኢትዮጵያ ክልል ከሚገኙ ዞኖችና ልዩ ወረዳዎች መካከል አንዷ ስትሆን ከመዲናችን አ/አ በሻሸመኔ 313ኪ/ሜ እንዲሁም በቡታጅራ 245ኪ/ሜ ርቀት ላይ ስትገኝ ከክልሉ ዋና ከተማ ሆሳዕና ደግሞ 80ኪ/ሜትር ርቀትላይ ትገኛለች፡፡በሀላባ ዞን ያለውን የተፈጥሮ መስህብ ከማስተዋወቃችን በፊት ስለ መስህብ ጥቂት መረጃ እንስጣችሁ መስህብ የሚባለው በተፈጥሮ ይዘቱና ውስጡ ባለው ማራኪና መሳጭ ተፈጥሮ አንድን የተለየ ጎብኚን የሚስብ የሚያስደንቅና የሚያጓጓ ድንቅ ሀብት ነው፡፡ተፈጥሮአዊ መስህብ በውስጡ ብሔራዊ ፓርኮችን፣ወንዞችን፣ሐይቆችን፣ፏፏቴዎችን፣ ፍል ውሃዎችን፣ተፈጥሮአዊ ዋሻዎችንና ሌሎችን ያልተጠቀሱ ጉዳዮችን የሚይዝ ማለት ነው፡፡ ጠቅለል ባለ ጉዳይ ላይ ይህን ያህል መረጃ ከጦቆምናችሁ በሀላባ ዞን ከሚገኙ በርካታ ተፈጥሮኣዊ መስህቦች መካከል ውስጥ አንዱ የሆነውን የደነቤ ፋማ ፏፏቴ /ፋማ መዝናኛ ማዕከል የቱሪስት መስህብ ስፍራን እናስተዋውቃቹሁ፡፡
የደነቤ ፋማ ፏፏቴ (ፋማ መዝናኛ)ከቁሊቶ ከተማ በ1.5 ኪ/ሜ ርቀት ላይ ይገኛል፡፡ ደነቤ ፋማ ፏፏቴ (ፋማ መዝናኛ) በውስጡ የተለያዩ አስደናቂና ማራኪ ገፅታ ያለው ሲሆን በተለይ የፏፏቴው ውሃ ወደ ታች በ12 ሜትር ርቀት ላይ እየወረደ ሲምዘገዘግ ላየው የአከባቢውን የተፈጥሮ ውበት ልዩ ያደርገዋል፡፡ ከዚህም በተጨማሪ በአከባቢው የሚሰማው የአዕዋፋት ዝማሬ እና የፏፏቴው ድምፅ በአንድ ላይ ተደምሮ አከባቢው መንፈስን የሚያድስና የአዕምሮ እርካታ የሚሰጥ ማራክና ውብ የመስህብ ቦታ ነው፡፡ ደነቤ ፋማ ፏፏቴ ከዚህ በፊት የተራቆተና ለአደጋ የተጋለጠ ስፍረ ነበረ፡፡ ነገር ግን መንግስትና የአከባቢው ማህበረሰብ ባደረጉለት የመልሶ ማልማት ሥራ አከባቢውን በተለያዩ ዛፎችና በተፈጥሮ ዕፅዋቶች ከመሸፈኑም ባሻገር ለተለያዩ አዕዋፋትና እንስሳት መገኛ መሆን ችሏል፡፡ መዝናኛውን ከዚህ በፊት የአከባቢው ህብረተሰብ ባለው የተፈጥሮ ውበት በመሣብ በዘልማድ ሄዶ የሚዝናናበት ስፍራ ቢሆንም ነገር ግን በ2000 ዓ.ም ሚሊንየምን ምክንያት በማድረግ ለወጣቱ ማህበረሰብ ብዙ የመዝናኛና የስራ ዕድል ለመፍጠር ታስቦ አዝናኝና ማራኪ በሆነ መልኩ ለመዝናኛነት ተሰርቷል፡፡ በአሁኑ ሰዓት በአከባቢው በጥሩ ሁኔታ የተሰራ የመዝናኛ ቤት ሲኖረው የተለያዩ ቅርፅ ያያዙ ባህላዊ መናፈሻዎቹ ለአከባቢው ልዩ ውበት አድማቂና መሳጭ እንዲሆን የራሳቸውን ድርሻ አበርክተዋል፡፡
በቁሊቶ ከተማና አከባቢው የመዝናኛ ስፍራ እጥረት የመኖሩን ያህል መዝናኛው ለወጣቱ ማህበረሰብ የሚሰጠው ፋይዳ ከፍተኛ ነው፡፡ ከዚህ ጋር በተያያዘ መዝናኛው ከዚህ በፊት አገልግሎት ለተወሰነ ጊዜ የሰጠ ቢሆንም አሁን ባለው ሁኔታ ግን የመዝናኛው አገልግሎት አሳጣጡ ላይ ውስንነቶች ያሉት በመሆኑ በዘርፉ ለመሰማራት የሚፈልጉ ማህበራትና ባለሀብቶች በዘርፉ ቢሰማሩ ትርፋማና ውጤታማ እነደሚሆኑ ጥርጥር ባለመኖሩ ይምጡና ኢንቨስት ያድርጉ፡፡ ይህን ድንቅ የተፈጥሮ ሀብታችንን ይምጡና ይጎብኙት መንፈሶን ያድሱበታል !!
ጎልጆ ተራራ ደን
የሀላባ ዞን በርካታ የሆኑ ባህላዊ፣ታሪካዊና ተፈጥሮኣዊ መስህቦች ይገኙበታል፡፡ ከተፈጥሮኣዊ መስህቦች አንዱ የሆነውን የጎልጆ ተራራ ደንን እናስተዋውቃቹ፡፡ ይህ ደን በሀላባ ዞን ዌራ ዲጆ ወረዳ ላይ ይገኛል፡፡ ደኑ በሀላባ ዙሪያ በሚገኘው የአንሾኮራ ቡጢ ቀበሌ ገበሬ ማህበር ልዩ ስሙ እናቱራስ በሚባል አከባቢ ይገኛል ፡፡የጎልጆ ተራራ ደን በአከባቢው ከሚያዋስኑት ቀበሌያት መካከል በሰሜን ምስራቅ ጢጣ ሊብጦራ፣በምዕራብ በንዶ ቀበሌ በደቡብ የኦሮሚያ ክልል ሻላ ወረዳ ያዋስናታል ፡፡ ጎልጆ የሚለውን ስያሜ ያገኘው የጣሊያን ጦር አዛዥ የሆነ አንድ ግለሰብ ስም እንደነበረና በተራራው አናት ላይ ጎጃሜ የሚባለው ስፈራ ደግሞ ጣሊያኑ ግለሰብ ጎጆ ሰርቶ የሚኖርበት እንደነበረ ከአከባቢው የአገር ሽማግሌዎች ለመረዳት ተችሏል፡፡ የጎልጆ ተራራ ደን በአከባቢው ህብረተሰብ ዘንድ የተለያዩ የአጠራር ስያሜዎች ያሉት ሲሆን ይህን ደን ልዩ የሚያደርገው አስደናቂና ዓይንን የሚያማልሉ የተፈጥሮ እፅዋትና የዱር እንስሳት መገኛ መሆኑ፣ የአቢያታና የሻላ ሀይቆች እንዲሁም ፓርኮች በአከባቢው የሚያዋስኑት መሆናቸውና መታየታቸው ማራኪ አድርጎታል ፡፡ በዚህ ,ደን ውስጥ የተለያዩ ውብና ማራኪ እዕፅዋት የሚገኙ ሲሆን ከነዚህም ውስጥ ጥድ፣ዌራ፣ክትክታ፣ግራር፣አጋምና እሬት እንዲሁም ያልተጠቀሱ ሌሎችንም ጨምሮ ልዩ ልዩ አይነት ዝርያ ያላቸው ግራሮችንና አንዳንድ አገር በቀል ዕፅዋቶች በስፍራው ይገኛሉ ፡፡
የጎልጆ ተራራ ደን ውስጥ የተለያዩ የዱር እንስሳት መገኛ መሆኑ ደግሞ እጅጉን ሳቢ ያደርገዋል፡፡ በመሰረቱ መስህብ የሚለው ቃል በራሱ በተፈጥሮአዊ ይዘቱና ውስጡ ባለው አስደናቂና መሳጭ ተፈጥሮ አንድን የተለየ ጎብኚን የሚስብና የሚማርክ እንዲሁም የሚያጓጓ ድንቅ ሀብት መሆኑ ይታወቃል፡፡ ከዚህ ጋር በተያያዘ በዚህ ደን ውስጥ ካሉት የዱር እንስሳቶች መካከል ጥቂቶቹን እንጠቁማችሁ እነርሱም ነብር፣አጋዘን፣ድኩላ፣አነር፣አዞ፣ጅብ፣ቀበሮ፣ጦጣ፣ዝንጀሮ እንዲሁም የተለያዩ አይነት የእባብ ዝርያዎችና ዔሊ፣ከሻላ ብሔራዊ ፓርክ የሚመጡ የተለያዩ ብርቅዬ አዕዋፋት መገኛ ከመሆኑ ጋር ተያይዞ ለመንፈስ እርካታ የሚሰጠውን ደስታ ወደር አይገኝለትም ፡፡ ከዚህም በተጨማሪ በጎልጆ ተራራ ደን አከባቢ የተለያዩ ቀለማት ያላቸው እንደ ነጭ፣ቀይና ዳለቻማ የቀለም ይዘት ያላቸው ጭቃማ አፈር ለቤት ቀለምነት ያገለግላሉ ፡፡ በአከባቢው የሻላ ጥግ ላይ የቦሌ ጨው መገኛ ከመሆኑ ጋር ተያይዞ የአከባቢው ማህበረሰብ ለከብቶቻቸውና ለልብስ ማጠቢያነት ሲጠቀሙበት ላየ ልዩ ያደርገዋል፡፡ .ይህንን ድንቅና ማራኪ የተፈጥሮ መስህብ ወደ ዞናችን በመምጣት ይጎብኙት