"ክብር ለጥበብ "በሚል መሪ ሀሳብ ለባህል የጥበብ ባለሙያዎች የእውቅና መርሃ ግብር በወልቂጤ ከተማ ተካሄድ።
"ክብር ለጥበብ "በሚል መሪ ሀሳብ ለባህል የጥበብ ባለሙያዎች የእውቅና መርሃ ግብር በወልቂጤ ከተማ በመካሄድ ላይ ነው።
የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ዋና አፈ ጉባኤ ወ/ሮ ፋጤ ሰርሞሎ እንደገለጹት የክልሉን ብሔር ብሔረሰቦች ባህል እና ታሪክ ከኢትዮጵያዊ ማንነት ጋር በማስተሳሰር ህብረ ብሔራዊ አንድነት እንዲጠናከር በትኩረት መስራት ይገባል ብለዋል።የክልሉ ህዝቦች ባህል፣ታሪክ፣እንዲተዋወቅ፣ህብረ ብሔራዊ አንድነታችን እንዲጎለብት፣ሀገራዊ መግባባት እና ብሔራዊ አንድነት እንዲጠናከር የኪነ ጥበቡ ዘርፍ የላቀ አስተዋጽኦ እንዳለው ተናግረዋል።የባህልና ቱሪዝም ሴክተር በክልሉ ባህላዊ እሴቶች እንዲጠኑ እንዲተዋወቁ እና እንዲለሙ በማድረግ ረገድ የተጣለበትን ኃላፊነት ለመወጣት እየሰራ ስለመሆኑም ዋና አፈ ጉባኤዋ አመላክተዋል።ክልሉ በተፈጥሮም ሆነ በብዝሀ የባህል ሀብት ጸጋ የተቸረው ነው ያሉት አፈ ጉባኤዋ ይህንን ብዝሀ ማንነት ማልማት እና ማስተዋወቅ ላይ በትኩረት መስራት እንደሚገባም አብራርተዋል።
የክልሉን የቱሪዝም ሀብት በማልማት ከዘርፉ ተጠቃሚ መሆን በሚቻልባቸው ጉዳዮች ላይ መስራት ተገቢ ስለመሆኑም ዋና አፈ ጉባኤዋ አመላክተዋል።የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል የባህልና ቱሪዝም ቢሮ ሀላፊ አቶ ሳሙኤል መንገሻ እንደገለጹት በክልሉ የሚገኙ የብሔር ብሔረሰቦችን ባህል፣ታሪክ እና ቅርስ የማልማት እና የማስተዋወቅ ስራ ላይ በልዩ ትኩረት እየተሰራ ነው ብለዋል።ባህል የማህበረሰቡ ሁለንተናዊ እንቅስቃሴ ነጸብራቅ ነው ያሉት አቶ ሳሙኤል የዘርፉን ጸጋዎችና መልካም እሴቶችን በማስተዋወቅ ረገድ የተጀመሩ ስራዎችን ማጠናከር እንደሚገባም ጠቁመዋል።የኪነ ጥበብ ዘርፉ የተለያዩ የባህል እሴቶች እንዲጎለብቱ ያለው ሚና የላቀ ነው ያሉት ኃላፊው ቢሮ በክልሉ የሚገኙ ብሔር ብሔረሰቦች ባህላቸው እና ታሪካቸው እንዲበለጽግ እየሰራ ስለመሆኑም አስረድተዋል።ህብረ ብሔራዊ አንድነትን ማጠናከር በሚቻልባቸው የባህል እሴቶች ላይ ትኩረት በማድረግ የህዝብ ተጠቃሚነትን ለማሳደግ እየተሰራ መሆኑን ነው አቶ ሳሙኤል ያስታወቁት።በክልሉ ያለውን የኪነ ጥበብ አቅም በአግባቡ መጠቀም የሚያስችሉ የሪፎርም ስራዎች ተግባራዊ እየተደረገ መሆኑን ኃላፊው አብራርተዋል።ኪነ ጥበብ ብሔራዊ መግባባት እና ጠንካራ ሀገረ መንግስት በመገንባት ሂደት የሚኖረው አበርክቶ የላቀ ስለመሆኑም አቶ ሳሙኤል አስረድተዋል።
የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ባህልና ቱሪዝም ቢሮ ምክትል ኃላፊና የባህል ዘርፍ ሀላፊ አቶ ደግነህ ቦጋለ ባቀረቡት የመወያያ ጽሁፍ እንደገለጹት "ክብር ለጥበብ" በሚል መሪ ሀሳብ ለኪነ ጥበብ ባለሙያዎች እውቅና የመስጠት መርሐ ግብር ዋነኛ አላማ የዘርፉ ባለሙያዎች ላበረከቱት ክልላዊ እና ሀገራዊ አስተዋጽኦ ነው ብለዋል።የክልሉ የባህል ኢንዱስትሪ እንዲጎለብት እና ለልማት የሚኖረውን ሚና በማሳደግ ረገድ የዘርፉ ባለሙያዎች ጥበባዊ አበርክቶው ከፍ ያለ መሆኑንም አቶ ደግነህ ጠቁመዋል።በክልሉ ለሁለተኛ ጊዜ በሚሰጠው የእውቅና መርሐ ግብር ከሁሉም ዞኖች እና ልዩ ወረዳዎች የተውጣጡ የኪነ ጥበብ ባለሙያዎች እንደሚገኙበት የተናገሩት አቶ ደግነህ በኪነ- ጥበብ እና ስነ ጥበብ ዘርፍ በርካታ የፈጠራ ዘውጎችን እንደሚያካትትም አብራርተዋል።
