Skip to main content

ኢትዮጵያ የመጀመሪያውን የዩኔስኮ ዓለም አቀፍ ጂኦፓርክ እውቅና አገኘች

ኢትዮጵያ የመጀመሪያውን የዩኔስኮ ዓለም አቀፍ ጂኦፓርክ እውቅና አገኘች

ጥቅምት 23/2019 ዓ.ም.

ኢትዮጵያ የመጀመሪያውን የዩኔስኮ ዓለም አቀፍ ጂኦፓርክ እውቅና ማግኘቷ በሀገሪቱ የቱሪዝም ዘርፍ ታሪካዊ ስኬት መሆኑ ተገለጸ።

በ11ኛው የዩኔስኮ ዓለም አቀፍ ጂኦፓርኮች ካውንስል (UNESCO Global Geoparks Council) መደበኛ ስብሰባ ላይ የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ስምጥ ሸለቆ ጂኦፓርክ (Central Ethiopia Rift Valley Geopark) የዩኔስኮ ዓለም አቀፍ ጂኦፓርክነት እውቅና እንዲያገኝ መጽደቁን የባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር አስታውቋል።

በዚህም ኢትዮጵያ ከሞሮኮ፣ ታንዛኒያና ቱኒዚያ በመቀጠል የዩኔስኮ ዓለም አቀፍ ጂኦፓርክ እውቅና ያገኘች አራተኛዋ የአፍሪካ ሀገር ሆናለች። የእውቅናውን ይፋዊ ሰርተፍኬት በአውሮፓውያኑ ኤፕሪል 27 እንደምትረከብም ይጠበቃል።

የዩኔስኮ ዓለም አቀፍ ጂኦፓርክ እውቅናው ኢትዮጵያ ያላትን ልዩ የጂኦሎጂካል ቅርስና የተፈጥሮ ሀብት በዓለም አቀፍ ደረጃ ለማስተዋወቅ ከፍተኛ ዕድል እንደሚፈጥር ተጠቁሟል። በተጨማሪም የምድር ሳይንስ ሀብቶችን ለሳይንሳዊ ጥናት፣ ለቱሪዝም ልማትና ለዘላቂ ልማት በማዋል የሀገሪቱን የቱሪዝም አቅም ለማሳደግ ወሳኝ ሚና ይኖረዋል።

በተለይም የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ስምጥ ሸለቆ ጂኦፓርክ እውቅና ማግኘቱ የአካባቢውን የጂኦሎጂካል ቅርሶችና ስነ-ምህዳራዊ ሀብቶች ለመጠበቅ፣ የአካባቢ ማኅበረሰቡን በዘላቂ ልማት ተጠቃሚ ለማድረግ፣ የሥራና የገቢ ምንጮችን ለመፍጠር እንዲሁም ዓለም አቀፍ ትብብርን ለማጠናከር አዳዲስ አማራጮችን ይከፍታል።

ኢትዮጵያ በተፈጥሮ፣ በታሪክና በባህል ቅርሶቿ ከምትታወቅበት የቱሪዝም አቅሟ በተጨማሪ በጂኦ-ቱሪዝም ዘርፍም አዲስ ምዕራፍ እንድትከፍት ይህ እውቅና አስተዋጽኦ እንደሚኖረው ተገልጿል።

የባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር ለዚህ ታሪካዊ ስኬት መመዝገብ አስተዋጽዖ ላበረከቱ ሁሉም ባለድርሻ አካላት፣ ባለሙያዎችና አጋር ተቋማት ምስጋናውን በማቅረብ፣ ለሀገሪቱ ሕዝብ እንኳን ደስ አላችሁ የሚል የደስታና የኩራት መልዕክት አስተላልፏል።

ይህ ስኬት የኢትዮጵያን የጂኦሎጂካል ቅርስ ለትውልድ ከመጠበቅ ባለፈ፣ ሀገሪቱን በዓለም የቱሪዝም ካርታ ላይ ይበልጥ ለማስተዋወቅና የማኅበረሰቡን የኢኮኖሚ ተጠቃሚነት ለማሳደግ የሚያግዝ ታላቅ ምዕራፍ ነው።

Image