የከምባታ ብሔር የ2019 ዓ.ም የዘመን መለወጫ "መሳላ" በዓል በዱራሜ ከተማ ሁለገብ ስታዲየም በከፍተኛ ህዝባዊ ትዕይንትና በደማቅ ኤግዚቢሽን ተከበረ።
የከምባታ ብሔር የ2019 ዓ.ም የዘመን መለወጫ "መሳላ" በዓል በዱራሜ ከተማ ሁለገብ ስታዲየም በከፍተኛ ህዝባዊ ትዕይንትና በደማቅ ኤግዚቢሽን ተከበረ።
በበዓሉ አከባበር ላይ የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ምክትል ርዕሰ መስተዳድር አቶ አንተነህ ፈቃደ፣ የክልሉ ህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ዋና አፈ ጉባኤ ወይዘሮ ፋጤ ሴርሞሎ፣ የክልሉ ብሔረሰቦች ምክር ቤት አፈ ጉባኤ አቶ አቡቶ አኒቶ፣ የከምባታ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ አረጋ እሸቱ እና የዞኑ ባህልና ቱሪዝም መምሪያ ኃላፊ አቶ መሐመድ ኤደሞን ጨምሮ በርካታ የፌደራል፣ የክልልና የዞን አመራሮች፣ የሀገር ሽማግሌዎች፣ ከአጎራባች አካባቢዎችና ከልዩ ልዩ ክልሎች የመጡ እንግዶች እንዲሁም የዞኑ ነዋሪዎች ተገኝተዋል።
አቶ አንተነህ ፈቃደ በንግግራቸው መሳላ የከምባታ ብሔር አኩሪ ታሪክ፣ ክብሩና የማንነቱ መገለጫ እንደሆነ ገልጸው፤ በዓሉ የቂም፣ የበቀልና የጥላቻ ማስወገጃ እንዲሁም የሰላምና የፍቅር መተሳሰቢያ በመሆኑ፣ በUNESCO የማይዳሰስ ባህላዊ ቅርስ ሆኖ እንዲመዘገብ የተጀመረው ጥረት ተጠናክሮ እንደሚቀጥል አረጋግጠዋል።
ወይዘሮ ፋጤ ሴርሞሎ በበኩላቸው በዓሉ ከአሮጌው ዘመን ጭንቀት ተላቆ በአዲስ ተስፋ የመስራት መንፈስን የሚያጠናክርና የሁሉም አካባቢዎች ህዝቦችን በአንድነት የሚያሰባስብ ወሰን ተሻጋሪ እሴት ያለው መሆኑን ጠቁመዋል።
የዞኑ ዋና አስተዳዳሪ አቶ አረጋ እሸቱ የመሳላ በዓል ከሰኔ ወር የእርሻ ዝግጅት ጀምሮ በመስከረም 1 "ሌንጃ" (ኤነሬ) የምትባለው ወፍ በሰማይ ላይ በመታየት የሚከናወን ረጅም ባህላዊ ስርዓት ያለው፣ የዞኑን የቀን አቆጣጠር ቀመር የሚያሳይና የደቦ ህብረት የሚንጸባረቅበት መሆኑን አብራርተዋል። በተጨማሪም ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ ወደ አምበሪቾ ተራራ በመምጣት በሀገር ሽማግሌዎች የተመረቁበት ግንቦት 25 ቀን ከዚህ በኋላ በየዓመቱ የዞኑ የምርቃት ቀን "ማሳ በሪ" ተብሎ መሰየሙን አብስረው፣ ህዝቡ በዕለቱ ተገኝቶ የምድሪቱንና የትውልዱን በረከት እንዲካፈል ጥሪ አቅርበዋል።
አቶ መሐመድ ኤደሞ በበኩላቸው በበዓሉ ዋዜማ የሚከናወነው የ"ሰጄ ጎቾ" የዕርቅና የፍትህ ስርዓት፣ የ"አተካና" ማዕድ መቋደስ፣ እናቶች ከበጋ ወራት ጀምሮ የሚያደርጉት ጥንቃቄና የ"ሼማታ" የቡድን ስራ የቤተሰብ ኃላፊነትን የሚያስተምር ታላቅ ትምህርት ቤት መሆኑን ገልጸው፣ ወጣቱ ይህን ባህል ተረክቦ ማዘመን እንዳለበት አሳስበዋል።
የበዓሉ አካል የሆነውና የግብርና ምርቶችን፣ የባህል ቁሳቁሶችንና ባህላዊ ምግቦችን ያካተተው ልዩ ኤግዚቢሽን በከፍተኛ አመራሮቹ ተመርቆ ለእይታ የበቃ ሲሆን፤ በመጨረሻም አመራሮቹ ለአዲሱ 2019 ዓ.ም የሰላም፣ የጤና፣ የአርሶ አደሩ ምርት የሚባረክበትና የኢትዮጵያ የከፍታ ዘመን እንዲሆን መልካም ምኞታቸውን በማስተላለፍ በደማቅ ሁኔታ ተከብሯል።
Saja, Ethiopia 

